Tuesday, August 13, 2013

ፍልሰታ ለማርያም




ምንጭ፡ www.ermiasnebiyu.org
ክፍል አንድ
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ከመሞቷ በፊት በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መቃብሩ ቦታ ትጸልይ ነበር።  መንፈስ ቅዱስም ለእመቤታችን ከዚህ ዓለም እንደምትለይ ነገራት።   ጌታችንም በደብረ ዘይት ላሉ ደናግላን ነግሯቸዋልና ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጥነት መጡ።  እርሷን መንፈስ ቅዱስ የነገራትን ነገረቻቸው።  እነሱም እንደመጡ ባየች ጊዜ እንዲህ ብላ ጸለየች። ‹‹ልጄ ወዳጄ፤ ፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ልመናየን ተቀብለህ ደቀ መዝሙርህን ዮሐንስን በዚህች ሰዓት አምጣው፤ እንዲሁም በሕይወት ያሉትንና በሕይወት የተለዩንን ቅዱሳን በሙሉ ወደ እኔም አምጣቸው።  አንተ የሕያዋን አምላክ ነህና፤ለአንተም ምስጋና ይሁን አሜን›› አለች።  በዚያን ጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ቅዱስ ዮሐንስን ደመና ተሸክማ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደረሰችው።  ቅዱስ ዮሐንስም እንደደረሰ ሰገደላትና በፊቷ ቆሞ እንዲህ አላት፤ ‹‹ሰላምታ ይገባሻል ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልደሽልናልና፤ ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ።  አንቺ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተሽ በክብር በምስጋና ወደ ዘለዓለም ሕይወት ትሄጃለሽና።››  እመቤታችንም ይህን በሰማች ጊዜ እጅግ ደስ አላት እንዲህ ብላ አምላኳንም አመሰገነችው።  ‹‹ጌታዬ አምላኬ ፈጣሪዬ ሆይ፤ ላንተ ክብር ምስጋና ይገባል።  የለመንኩህን ሰጥተኸኛልና።  አሁንም ነብሴን ተቀብለው ወደ ሰማይ ወደ አንተ ሊይሳርጓት ከሚመጡ መላእክቶችህ ጋር በመምጣትህ የምለምንህን ሁሉ ስጠኝ።›› በዚህን ጊዜ ከሰማይ እንዲህ የሚል ድምጽ መጣ፤ እነሆ አሁን መላእክት ይደርሳሉ።  ቅዱሳን ሐዋርያትም ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ይደርሳሉ።  ቅዱሳን ሐዋርያት ከዚህ ዓለም የተለዩትም፤ በሕይወት ያሉትም ሁሉ በአንድነት መጥተው ለእመቤታችን ሰገዱላት።  እነርሱም አመሰገኗት እንዲህም አሏት። 
‹‹ጸጋን የተመላሽ ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይብልሽ ፈጣሪያችን ከዚህ ዓለም ለይቶ ቃል ኪዳን እንደሰጠሽ በክብር በምስጋና ከእርሱ ጋር ያሳርግሻልና አሏት።››  በዚህን ጊዜ እመቤታችን በአልጋዋ ላይ ተቀመጠች።  ቅዱሳን ሐዋርያትንም እንዲህ አለቻቸው።  ‹‹ፈጣሪዬ ፈጣሪያችሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እኔ እንደሚመጣ እናንተንም እንዳየኋችሁ እንደማየው አሁን አወኩ። ከዚህ ከሥጋዬ ወጥቼ ወደ  ዘለዓለም ሕይወት እሔዳለሁ።  ነገር ግን እናንተ እኔ ከዚህ ዓለም እንደምለይ ማን ነገራችሁ? አወቃችሁ?››   ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱሳን ሐዋርያት በሙሉ ወደ አንቺ እንመጣ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ አዘዘን፤ መጣን አሏት።  እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ይን ነገር ከቅዱሳን ሐዋርያት በሰማች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ አምላኳን አመሰገነች።  እንዲህም አለች ‹‹ከእንግዲህ ወዲያ ትውልድ ሁሉ ያከብሩኛል ያመሰግኑኛል።››  ይህን ብላ እንደጨረሰች እጣን አምጥታችሁ በማጠን የፈጣሪዬን ስም ጥሩት አለቻቸው።  እነሱም እንደታዘዙት አደረጉ።  በዚህን ጊዜ ጌታችን ተገልጾ ብዙ ድንቅ ተአምራትን አደረገ።  በሽተኞች ወደ እመቤታችን ወደ አለችበት ቤት በቀረቡ ጊዜ ከደዌአቸው ይፈወሱ ነበር።  እመቤታችን ከሥጋዋ የምትለይበት ሰዓት ሲደርስ ቅዱሳን ሐዋርያትንና ደናግልን ትባርካቸው ዘንድ እያለቀሱ ለመኗት።  እመቤታችንም እጇን ዘርግታ ባረከቻቸው።  በዚህን ጊዜ ፈጣሪያችን ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ በመለኮታዊ እጆቹ ይዞ በብርሃን ልብስ አጎናጽፎ ወደ ከፍተኛ መኖሪያ ከእርሱ ጋር አሳረጋት።  ሥጋዋን ግን እንደሚገባ ገንዘው፤ ወደ ጌቴ ሴማኒ ተሸክመው እንዲወስዷት ሐዋርያትን አዘዛቸው።  ነፍሷ ከሥጋዋ ከመውጣቷ በፊት በሰው አንደበት ይህ ነው ተብሎ የማይነገር ብርሃን እያየች ነበር።  እመቤታችንም ፈጣሪዋን ልጇን ወዳጇን እንዲህ ብላ ጠየቀችው። ‹‹ልመናየን ትሰማ ዘንድ እለምንሃለሁ።  በስሜ ወደ አንተ የሚለምነውን ሁሉ፤ ልመናውን ተቀበለው በመከራም ውስጥ ሁኖ ስሜን ጠርቶ ወደ አንተ የሚለምነውን ከመከራም ሁሉ አድነው፤ በሰማይም በምድርም በሥራው ላይ ሁሉ አንተ ከሃሊ ነህና መታሰቢያየን በውስጧ የሚያደርጉባትን የሁሉንም መስዋእታቸውን ተቀበል።›› ፈጣሪም እንዲህ ብሎ መለሰላት።  የለመንሽኝን ሁሉ አደርግልሻለሁ።  እመቤታችንም ከአረፈች በኋላ ጌታችን እንዳዘዘ ወደ ጌቴ ሰማኒ ሊወስዷት ሐዋርይት ገንዘው ተሸከሟት።  አይሁድም በሰሙ ጊዜ ሥጋዋን ሊይቃጥሉ መጡ።  ከእነርሱም አንዱ ከምድር ይጥላት ዘንድ የእመቤታችንን አልጋዋን ያዘ።  ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እጆቹን በእሳት ሰይፍ ቀጣውና እጆቹ በአልጋው ላይ ተንጠለጠሉ።  ያን ጊዜ በጌታችን አምኖ ወደ እመቤታችን እያለቀሰ እንዲህ እያለ ለመነ።  የእውነተኛ አምላክ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እናት አንቺ በእውነት ድንግል የሆንሽ በእኔ ላይ ይቅርታ ታደርጊ ዘንድ አለምንሻለሁ።  በሐዋርያትም ልመና እጆቹ ተመልሰው እንደቀድሞው ደህና ሆኑ።  እመቤታችንን  በቀበሯት ጊዜ ከዚያ ሶስት ቀን ኖሩ እረፍቷም የነበረው እሁድ ቀን ጥር 21 ነበር።  ጌታችንም ብርሃናውያን መላእክትን ልኮ ሥጋዋን ከመቃብር ወስደው በገነት ውስጥ በዕፀ ሕይወት ሥር አኖሯት።  ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ግን ያን ጊዜ አልነበረም በደመና ላይ ተጭኖ እርሱ ሲመጣ መላእክት ሲያሳርጓት እመቤታችንን አገኟት   መላእክትም ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ድንግል ማርያም እጅ ንሳ አሉት:: እርሱም ሰገደላትና ተሳለማት ከእርሷም ተባረከ:: ከዚህም በኋላ ወደ ሐዋርያት ደረሰ።  እነርሱም እመቤታችንን ማርያምን እንደ አረፈችና እንደ ቀበሯትም ነገሩት።  ቅዱስ ቶማስም ሥጋዋን እስከ ማይ አላምንም አላቸው።  ሥጋውንም ያሳዩት ዘንድ ወደ መቃብሯ በአደረሱት ጊዜ ከመቃብሩ ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም:: ደንግጠውም አደነቁ::  ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችን እንዳገኛት ነገራቸው።  ቅዱሳን ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ የእመቤታችንን ዕርገቷን  ስላላዩ እጅግ አዘኑ ሥጋዋን በምድር ውስጥ ይተው ዘንድ እንዳልወደደ መንፈስ ቅዱስ አስገነዘባቸው።  ከዚህም በኋላ አንድ ጊዜ ደግሞ እርሷን ያሳያቸው ዘንድ እንዳለው ጌታችን ቃል ኪዳን በማድረግ ተስፋ ሰጣቸው።  እነርሱም እስከ ነሐሴ 16 ቀን በተስፋ ኖሩ።  የእመቤታችንም የእድሜዋ ዘመን 64 ዓመት ነው። በአባትና በእናቷ ቤት 7 ወር፤ በመቅደስም 12 ዓመት፤ በዮሴፍም ቤት 34 ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ ዕርገት በኋላ በወንጌላዊ ቅዱስ ዮሐንስ ቤት 14 ዓመት ነው።
ይቆየን…………….
የሕይወት የድህነት አለኝታ የሆነች እርሷን እናቱን ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።
የእመቤታችን በረከቷና ረድኤቷ ይደርብን አሜን::

No comments:

Post a Comment