በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ
አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
መግቢያ
አሠርቱ ትዕዛዛት በሊቀ ነቢያት ሙሴ ዘመን ወይም ከዚያም ቀድሞ ለነበሩት ብቻ ሳይሆን በየዘመናቱ ለሚነሱ የሰው ወገኖች ሁሉ የተሰጡ ሰማይና ምድር እስኪያልፉ (ዕለተ ምጽአት) ተጠብቀው የሚኖሩ ትዕዛዛት ናቸው፡፡ “ እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ። እንግዲህ ከነዚህ ከሁሉ ካነሱት ትእዛዛት አንዲቱን የሚሽር ለሰውም እንዲሁ የሚያስተምር ማንም ሰው በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ ታናሽ ይባላል፤ የሚያደርግ ግን የሚያስተምርም ማንም ቢሆን እርሱ በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይባላል።” እንዳለ ማቴ 5፣18-19፡፡
እነዚህ ትዕዛዛት በክርስትና ሳይለወጡ ይልቁኑ ሰፍተውና ተብራርተው ጸንተውም ይገኛሉ፡፡“ለቀደሙት። አታመንዝር እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።” ማቴ 5፣20–48፡፡ “የሥራህን ሁሉ ፍጻሜ አየሁ ትእዛዝህ ግን እጅግ ሰፊ ነው። አቤቱ፥ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ! ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው።” መዝ 118(119)፣96–97፡፡ እግዚአብሔር እነዚህን አሥርቱን ትዕዛዛት በጣቶቹ በመጀመሪያ ለሙሴ በሰጣቸው ቀጥሎም ለእምነቱ ባለው ቅንዓት ሙሴ በሰበራቸው ምትክ አድርጎ ባዘጋጃቸው በሁለቱ ጽላቶች ላይ በመጻፍ ቀድሞ ለእስራኤል ዘሥጋ በመቀጠልም ለእስራኤል ዘነፍስ ለክርስቲያኖች ሰጥቷል፡፡ ዘጸ 20፣1-17፣ ዘዳግም 5፣1-ፍፃሜ፡፡
አሠርቱ ትዕዛዛት በጠቅላላው ስንመለከታቸው የሚከተሉትን ዋና ዋና ነጥቦች እንድንረዳ ያደርጉናል፡፡
1. በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የተደረገ ኪዳን ነው፡፡
አሠርቱ ትዕዛዛት በሊቀ ነቢያት ሙሴ ዘመን ወይም ከዚያም ቀድሞ ለነበሩት ብቻ ሳይሆን በየዘመናቱ ለሚነሱ የሰው ወገኖች ሁሉና ዛሬም ለምንገኘው ለክርስቲያኖችም የተሰጡ ሰማይና ምድር እስኪያልፉ (ዕለተ ምጽአት) ተጠብቀው የሚኖሩ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የተደረገ ኪዳን እንዲሁም ለሰውም የተሰጡ ትዕዛዛት ናቸው፡፡ “አምላካችን እግዚአብሔር በኮሬብ ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። እግዚአብሔር ዛሬ በዚህ በሕይወት ካለነው ከእኛ ከሁላችን ጋር እንጂ ከአባቶቻችን ጋር ይህችን ቃል ኪዳን አላደረገም።” እንዳለ ዘዳግም 5፣2-3፡፡
ትዕዛዛቱ የተጻፉባቸው ሁለቱ ጽላቶችም “የቃል ኪዳኑ ጽላቶች” ዘዳግም 9፣11 ሲባሉ መጽሐፉም
የቃል ኪዳኑ መጽሐፍ ተብሏል፡፡ ዘጸ 24፣7፡፡ እነዚህን ትዕዛዛት ታላቅነታቸውን እንረዳ ዘንድ በሲና ተራራ ላይ ተራራው እየጤሰ፣ በደመና ተከቦ፣ የመለከትና የእምቢልታ ድምጽ እየተሰማ ለሙሴ ሰጥቶታል፡፡ “ሙሴም፦ እጅግ እፈራለሁ እንቀጠቀጥማለሁ እስኪል ድረስ የሚታየው እጅግ የሚያስፈራ ነበር፡፡” ዕብ 12፣21፣ ዘጸ 19፣16-19፡፡ ይህም ትዕዛዛቱ ምን ያህል ታላቅ እንደሆኑና መፈጸምም ግዴታ እንደሆነ የሚያመለክት ነው፡፡
2. የትዕዛዛቱ አስፈላጊነት
እነዚህ ትዕዛዛት በእግዚአብሔር አንደበት የተነገሩና ዘጸ 20፣ በሁለቱ
ጽላቶች ላይ በእጆቹ የተጻፉ ዘዳግም 19 መሆናቸው ተፈላጊነታቸውን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴም አሥርቱን ትዕዛዛት ተቀብሎ
ከተራራው ሲወርድ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት ከአቀረበ በኋላ ደሙን ወስዶ በሕዝቡ ላይ ረጭቶታል፡፡ ዘዳግ 24፣4-8፡፡ እነዚህ
ትዕዛዛት በእግዚአብሔር ጣቶች ከአንድ ጊዜ በላይ መጻፋቸው አስፈላጊነታቸውን የሚያጎላው ነው፡፡ ዘዳግም 20፣2-17፣ ዘዳግም
5፣6-21፣ ዘዳግም 10፣41፣ ዘጸ 34፣1
3. የትዕዛዛቱ ቁጥር አሥር ስለምን ሆነ?
በዕብራውያን አሥር ቁጥር የፍጹምነት ምሳሌ ነው፡፡ ትዕዛዛቱ አሥር ቢሆኑም
የሕግጋትና የትዕዛዛት ምሳሌ መሆናቸውን ለማመልከት ነው፡፡ የአሥር ቁጥርን የፍጹም ነገር ምሳሌነት በጥቂቱ እንመልከት፡-
• የአሥሩ
ደናግል ምሳሌ፡‑ ማቴ 25፣1-12፡፡ በዚህ ምሳሌ አሥር ቁጥር ጻድቃንንም ኃጥአንንም - መላውን ዓለም ያመለክታል፡፡
• አሥር
ምናን የተሰጣቸው ባሪያዎች ምሳሌ፡‑ ሉቃ 19፣13-17፡፡ እነዚህ አሥሩ ባሮች ጌታቸው እስኪመጣ ድረስ ነግደው እንዲያተርፉ
ገንዘቡን የሰጣቸውን ጻድቃንና ኃጥአን ይወክላሉ፡፡
• የጠፋው
ድሪም ሉቃ 15፣8፡፡
ነቢዩ ዳንኤል “እኛን ባሪያዎችህን አሥር ቀን ያህል ትፈትነን ዘንድ እለምንሃለሁ የምንበላውንም
ጥራጥሬ የምንጠጣውንም ውኃ ይስጡን፡፡” ዳን 1፣12 የቁጥሩን
የፍጹም ነገር ምሳሌነት ያመለክታል፡፡ ዘፍጥ 31፣7፤ ኢዮብ 19፣3፡፡ ለአሥር ቁጥር የተነገረው ሁሉ ለብዜቶቹ (መቶ፣ ሺህ፣ …) ይነገራል፡፡ ሉቃ 15፣4፣ 1ኛ ቆሮ 14፣19፡፡
4. ሁለቱ ጽላቶች
አሠርቱ ትዕዛዛት በሁለቱ ጽላቶች ተጽፈው የሚገኙ ትዕዛዛት ናቸው፡፡ በአንዱ
ጽላት ላይ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግኑኝነት የሚያመለክቱ ሦስት ትዕዛዛት በሌላኛው ጽላት ላይ ደግሞ ሰዎች ከሰዎች ጋር
እርስ በርስ በሚኖራቸው ግኑኝነት ላይ የታዘዙ ሰባት ትዕዛዛት ይገኛሉ፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአንድ ሕግ አዋቂ በሰጠው
ምላሽ “ጌታ አምላክህን
በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥
እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ጸንተዋል።” ያለው ይህንኑ ሊያመለክተን ነው፡፡ ማቴ 22፣36-40፡፡
5. ሕገ ልቦናን ያስታውሱናል፡፡
አሠርቱ ትዕዛዛት በእግዚአብሔር ጣቶች ከመጻፋቸው አስቀድሞ በሕገ ልቦና
አባቶቻችን ይመሩባቸው እንደነበር ያስታውሱናል፡፡ ለምሰሌ፡-
•አትግደል፡-
መግደል ቀድሞም ቢሆን ኃጢአት እንደነበር ቃየን ወንድሙ አቤልን በገደለው ጊዜ በተቀጣው ከባድ ቅጣት ተገልጧል፡፡ ዘፍጥ 4፣13፡፡
• አታመንዝር፡-
ጻድቁ ዮሴፍ የጲጥፋራ ሚስት በዝሙት ወጥመድ አስገድዳ በያዘችው ጊዜ “ለዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም ሚስቱ ስለ ሆንሽ ከአንቺም በቀር
ያልሰጠኝ ነገር የለም እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? በእግዚአብሔር ፊት እንዴት ኃጢአትን እሠራለሁ?” ማለቱ በሕገ ልቦና ዘመን የሚታወቅ ሕግ መሆኑን ያመለክታል፡፡
•አትስረቅ
ዘፍጥ 31፣30-39፣ አትመኝ እዮብ 31፣1፣ ሰንበትን አክብር ዘዳግም 16፣23-29፣ ዘፍጥ 2፣2-3 … በሕገ ልቦና የሚታወቅ እንደነበር የሚያመለክቱ ናቸው፡፡፣
ለሊቀ ነቢያት ሙሴ የተሰጡት አሠርቱ ትዕዛዛት የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ፡፡
ዘጸ 20፣2-3፡፡
2. የእግዚአብሔር የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ፡፡ ዘጸ 20፣7፡፡
3. የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ አክብረውም፡፡ ዘጸ 20፣10፡፡
4. አባትህንና እናትህን አክብር፡፡ ዘጸ 20፣12፡፡
5. አትግደል፡፡ ዘጸ 20፣13፡፡
6. አታመንዝር፡፡ ዘጸ 20፣14፡፡
7. አትስረቅ፡፡ ዘጸ 20፡15፡፡
8. በሐሰት አትመስክር፡፡ ዘጸ 20፣16፡፡
9. አትመኝ፡፡ ዘጸ 20፣17፡፡
10. ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ፡፡ ዘሌ 19፡18፡፡
አንዳንድ ሊቃውንት ‹‹የተቀረጸውን ምስል ለአንተ አታድርግ›› የሚለውን ዘጸ 2፣5 እንደ ሁለተኛ ትእዛዝ በመውሰድ እስከ አትመኝ ድረስ
ያለውን አሥር በማድረግ ‹‹ባልንጀራህን እንደራስህ
ውደድ›› የሚለውን ዘሌዋ
19፣18 ያስወጡታል፡፡ ሌሎቹ ሊቃውንት ደግሞ ‹‹የተቀረጸውን ምስል ለአንተ አታድርግ›› የሚለው አምልኮን ስለሚመለከትና ‹‹ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ›› በሚለው ውስጥ ስለሚጠቃለል ለብቻው ሊመዘገብ አይገባውም፡፡ ይልቁኑ ጌታችን
በሚያስተምርበት ጊዜ ስለትዕዛዛት የቀረበለትን ጥያቄ ሲመልስ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ።
ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው
ናት። በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ጸንተዋል።” ማቴ 22፡35-40፡፡ በማለት ፍቅረ ቢጽን እንደ ዋነኛ ትዕዛዝ መቁጠሩን
ስላመለከተን አሥረኛው ትዕዛዝ ዘሌ 19፣18 ነው ይላሉ፡፡
የመጀመሪያው ትእዛዝ
“ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ።
ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ። በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም
ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ። አትስገድላቸው፥ አታምልካቸውምም በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና እስከ አራተኛ ትውልድ
ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ
እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና።” ዘጸ 20፣2-5፡፡
አምላካችን እግዚአብሔር ፈጽሞ የሚወደን መሆኑን ‹‹እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፡፡›› በማለት ገልጾልናል፡፡ እግዚአብሔር ራሱን ለሰዎች በተለያየ መንገድ ገልጧል፡፡
“ደግሞም፦ እኔ የአባትህ
አምላክ፥ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ አለው። ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ያይ ዘንድ ፈርቶአልና ፊቱን
ሸፈነ።” ዘጸ 3፣6፡፡
እግዚአብሔር ራሱን ‹‹ ሰማይንና ምድርን የሠራሁ፣ ብርሃንን፡ ሰውን፣ እንስሳትን፡ እፅዋትን… የፈጠርሁ እኔ ነኝ›› ወይም ‹‹እኔ ምንም ምን የማይወስነኝ አምላክ ነኝ፣ ከባርነት ያወጣኋችሁ መሆኔን
ዘነጋችሁትን?›› በማለት በማስፈራራት
የገለጠ አይደለም፡፡ ነገር ግን ፍቅሩንና ርኅራኄውን በማሳየት እኛም ይህን ለእኛ ያለውን ፍቅሩን፣ ቸርነቱን፣ ርኅራኄውን በተረዳን
ጊዜ
እንወደውና ፍቅርን ስለ ፍቅሩ እንድንሰጥ በሚያደርግ መልኩ ራሱን ገለጠልን
እንጂ፡፡ እግዚአብሔር ዘወትር ከሚያስደነግጠን ቃል ይልቅ ‹‹እኔ ከተለያዩ ደዌያት የፈወስሁህ፣ በዚህ ዓመት በሕይወትህ የተሳካልህ እንድትሆን
የፈቀድሁልህ፣ ከተለያየ ችግር ነጻ ያወጣሁህ፣ ከመከራም ያዳንሁህ፣ በጎውን ሁሉ ያደረግሁልህ አምላክህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፡፡›› በማለት ስለ አስፈሪነቱ ሳይሆን ስለ ፍቅሩና ይቅርታው እንዳንረሳው ስለሚሻ አምላክነቱን ገለጠልን፡፡
እኛ እግዚአብሔርን የምንሻውን በምንጠይቅበትና የምንሻውንም ከማግኘታችን
አስቀድሞ ብናስታውሰውም ከተቀበልን በኋላ እንረሳዋለን፡፡ ስንቸገር እንጠራዋለን ችግራችን ሲፈታ እንረሳዋለን፤ ሲርበን ሲጠማን እንጠራዋለን
ስንጠግብ ስንረካ እንረሳዋለን፤ ይህን ደካማነታችንን ስለሚያውቅ ያደረገልንን የቸርነት ሥራውን ሲነግረን በቀላሉ እናስታውሳለንና
ያደረግሁላችሁን እያሰባቸሁ አምልኩኝ ለማለት ፍቅሩንም እያሰብን ከፍቅር በመነጨ አምልኮ እንድናመልከው ጭምር አምላካችሁ እኔ ነኝ
ብሎ ተናገረን፡፡
ለእኛ ‹‹ በዘመኔ ሁሉ ቸርነትህን ያደረግህልኝ አምላኬ ሆይ ተናግሬም ሆነ ዘርዝሬ
ስለማልጨርሰው ቸርነትህ አመሰግንኻለሁ እገዛልኻለሁም›› ማለታችን ምንኛ
በፊቱ ያማረ ነው፡፡ ለጸሎት ቆመን ይህን፣ ያንም አደረግኽልኝ ቸርነትህንም ፈጽሜ አልረሳውም… ዘንግቸው ስለፍቅርህ ብደክም እንኳ ፈጽሜ ስለ ኃጢአቴ በማፈር ንስሐ እገባለሁ እንል ዘንድ ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ትዕዛዛቱን
በዚህ መልክ ለእኛ መግለጡ ምንኛ መልካም ነው! እግዚአብሔር የፍቅር
አምላክነቱን አምነንና አውቀን እንጂ ከፍርሀት የተነሳ እንድናመልከው የሚሻ
አይደለም፡፡ ‹‹እግዚAብሔር አምላክህ
እኔ ነኝ የሚለው›› የሚያመለክተው
አምልኮን ነው፡፡ ማቴ 4፣10፣ ኢያ 24፣15፡፡ አምልኮም ዘወትር በእግዚአብሔር ቤት እየተገኙ መጸለይን፣ መጾምን፣ መስገድን፣
ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብንና ትርጉም መረዳትን፣ መዘመርን ወዘተ የሚያካትት ነው፡፡ ይህን የማያደርግ ማንኛውም የሰው ወገን ‹‹እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ›› በሚለው ኃይለ ቃል ይወቀሳል፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለት የሚገባውን
አምልኮት ሊያቀርብለት ይገባዋልና፡፡
‹‹እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ›› የሚለው የፍቅሩ መግለጫ ኃይለ ቃል ነው፡፡ “ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም፤ ባርያ ጌታው የሚያደርገውን አያውቅምና፤
ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ፡፡” ዮሐ 15፣15
ባሮች ሳይሆን ወዳጆች እንዳለን፣ በጸሎትም ‹‹አባታችን…›› በሉኝ እንዳለ አስቀድሞ ወዶናልና እንወደዋለን፡፡ 1ኛ ዮሐ 4፣19፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደነገረው ከቀድሞ ጀምሮ ይህን ፍቅር
ይሻው ነበር፡፡ “እስራኤል ሆይ፥
ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም
ኃይልህ ውደድ።” ዘዳግም 6፣4-5፡፡
እግዚአብሔር ልቦናንና ፍቅርን፣ በልባዊ ፍቅር ላይም የተመሠረተውን እንጂ የታይታ አምልኮትን አይሻም፡፡ ስለዚህም እስራኤላውያንን
ስለ ኃጢአታቸው “ጌታም፦ ይህ ሕዝብ
በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈርቹም ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና፡፡” ኢሳ 29፣13፣ “ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፥ ልቡ ግን ከእኔ በጣም የራቀ ነው፤ የሰውም
ሥርዓት የሆነ ትምህርት እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል ብሎ በእውነት ትንቢት ተናገረ።” ማቴ 15፣8፡፡ ላይ እንደተገለጸው የወቀሳቸው፡፡
እንዴት ልናመልከው እንደሚገባ ሲናገርም “ልጄ ሆይ፥ ልብህን ስጠኝ፥ ዓይኖችህም መንገዴን ይውደዱ” ምሳ 23፣26 ሲል
ገልጧል፡፡ ስለዚህ ‹‹እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ›› የሚለው የሚለው ለእግዚአብሔር እንድንታዘዝ፣ እንድናመልከውም
የሚያደርገንና የሚያበረታታን ሕይወታችንንም እንድንሰጠው የሚያስገነዝበን
ነው፡፡ ከዚህ በማስከተልም ከፍቅር የተነሳ ያደረግሁላችሁን ሁሉ እያሰባችሁ የምታመልኩኝ አምላካችሁ እኔ ነኝና ‹‹ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ…›› አለን፡፡ እነዚህም ሌሎች የተባሉ አማልክት፡- ገንዘብ፣ መልካም ያደረጉልን፣ ዝና፣ መሪዎች ወይም ታላላቆች፣ ዓለምና የዓለም ፍላጎት፣
ራስን ማምለክ፣ ዓለምና መሻቱ፣ ክህደት፣ ሰይጣን … ናቸው፡፡
ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
kale hiwot yasemalin
ReplyDeleteKale Hiwoten yasemah Egziabher abzeto yebarkeh
ReplyDeleteእውነት ለመናገር በጣም ጥሩ ጽሁፍ ነው የእ/ር ቃለን በማጣቀሻነት መጠቀምህ የበለጠ እንደወደው አድርጓኛል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አብዝቶ ይባርክህ!!!!!!
ReplyDelete