Thursday, November 1, 2012

አዲሳባ... አዲሳባ...



ገና የኔ ቢጤ ከእንቅልፉ ሳይነቃ የአቃቂ ቅጥቅጥ ቼንቶዎችና ረዳቶቻቸው በአንድነት የተኛውን ለማንቃት በሚመስል ሁኔታ ጩኸታቸውን ይለቁታል፡፡ ቼንቶዎቹ በጡሩምባቸው፣ረዳቶቹ በአፋቸው፡፡ ጳራም… ጳራም… ጳራም… አዲሳባ… አዲሳባ… ሳሪስ አቦ ለገሃር፡፡ እነኚህ በራሪዎቹ ናቸው፡፡ በአንፃሩ ፈጣን ናቸው፡፡ ምክንያቱም መንገድ ሳይዘጋጋ በየቦታው ሳይገተሩ ስለሚሄዱ ነው፡፡ ከጠዋቱ 1ሰዓት ጀምሮ የሚገኙቱ ደግሞ በፍጥነታቸው ከኤሊ የሚሻሉት ሞተርና ጎማ ስላላቸው ብቻ ነው፡፡ ከሚሄዱት ፍጥነት በላይ የሞተራቸውና የረዳቶቻቸው ጩኸት ናላ ያናጋል፡፡ “እዛ ጋር ጠጋ በል” “አንተ ብረት ተደግፈህ የቆምከው ወይ እለፍ ወይ ሰው አሳልፍ” “አንቺ ደግሞ በጎን ገባ በይ”… ሞላ አያውቁም ሰው ካገኙ እንደ ዱቄት ይጠቀጥቃሉ፤ያጭቃሉም፡፡
በነዚህ መኪኖች አዘውትሮ እንደኔ ተጓዥ የሆነ ሰው አፍ አውጥቶ ባይጸልይም በልቡ ግን “ማርያም ማርያም” ማለቱ አይቀርም፡፡ ለምን ቢሉ ረዳቱ ከመኪናው ፍጥነት በተሻለ ሒሳቡን ከሰበሰበ በግማሽ ሰከንድ ልዩነት አጉል ቦታ መኪናው ቀጥ ሊል ይችላልና ነው፡፡ ለምን ቀጥ ይላል?  ነዳጅ ጨርሶ አልያም ችንጋ ተፈቶ ነው፡፡ ጠዋት መሆኑን ልብ ይሏል ታድያ፡፡ በዚህም ተገልጋዩ ይበሳጫል፡፡ ለገንዘቡ እንዳይምስላችሁ የሚበሳጨው ሌላ አማራጭ ትራንስፖርት የማይገኝበት ቦታ ለመውረድ ስለሚገደድ እንጂ፡፡ ከጉዳዩ መስተጓጎሉ ደግሞ ይብሳል፡፡

በየቀኑ እነዚህን ቼንቶዎች የሚጠቀም የኔ ቢጤ ሠርቶ አደርና አንዲሁም ተማሪ መኪኖቹን ከነ ሙሉ እቃቸው አብጠርጥሮ ያውቃቸዋል፡፡ ሾፌሮቹንና ረዳቶቻቸውንም ከነስማቸው ጭምር፡፡ ከዚህም የተነሳ አማራጭ ያጣ ዕለት ካልሆነ በጭራሽ የማይሳፈርባቸው መኪኖች አሉ፡፡ አማራጭ ሲጠፋ ግን በድብድብ ይሳፈራቸዋል፡፡‘ቢያንስ ነገ ጠዋት መድረሳቸው ስላማይቀር’፡፡ ለነገው ትምህርት ወይም ሥራ ያለጥርጥር ይደርሳሉ፡፡

ግርምት ቁጥር 1

አዲሳባ አዲስአባ

ከአቃቂ ለገሃር 17.5 ኪሎ ሜትር እንደሆነ በቅርቡ ለነዚሁ ቼንቶዎች ከትራንስፖርት ቢሮ በተሰጣቸው የታሪፍ መዘርዝር ላይ ለማየት ችያለሁ፡፡ ስለዚህ አቃቂ የአዲስ አበባ አካል ነች ማለት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ መስተዳድር ውጭ ከነበረች አላውቅም፡፡ እኔ ለአቃቂ ፀጉረ ልውጥ ነኝ፡፡ መጤ፡፡ እና  ለምንድን ነው ለገሃር ሳሪስ ከማለት ይልቅ አዲሳባ አዲሳባ የሚሉት? ግርምቴን ያባሰው ደግሞ ከረዳቶቹ አልፎ ነዋሪው  ሁሉ ከአቃቂ ሲነሳ ወይም ከለገሃር አልያም ከሳሪስ ይሳፈር በተንቀሳቃሽ ስለኩ ደውሎ ወይም ተደውሎለት እንደሁ “ወደአዲሳባ እየሄድኩ ነው” አልያም “ከአዲሳባ እየመጣሁ ነው” ሲል ትሰሙታላችሁ፡፡ ምናልባት እኔ ተሳስቼ እንደሁ ብዬ የዋና ሳጅንን የትራፊክ ሪፖርት ደጋግሜ ሰምቻለሁ፡፡ እሳቸው ግን ከኔ የተለየ ሲናገሩ አልሰማኋቸውም፡፡ “በአቃቂ ቃሊቲ” ይላሉ እንጂ “በኦሮምያ ልዩ ዞን” ብለው አያውቁም፡፡ አቃቂ አዲሳባ ባትሆን ኖሮ ከዋና ሳጅን ይልቅ በዋና ኢኒስፔክተር ስትጠራ በሰማን ነበር፡፡ ስለዚህ አቃቂዎች አዲሳባ ውስጥ ሆናችሁ አዲሳባ አዲሳባ አትበሉ፡፡

ግርምት ቁጥር 2

ከተማ ነኝ

ከዛው ከአቃቂ ሳትወጡ በእግር ነፋስ ለመቀበል የሚቀጣጠሩ ሰዎችን ጠጋ ብላችሁ ብትሰሟቸው እስቲ ከተማ ደረስ ብለን እንምጣ ሲባባሉ ታደምጣላችሁ፡፡ እነሱ ከቆሙበት አሥር እርምጃ አይርቅም ከተማ ብለው የሚጠሩት፡፡ ለምን ከተማ እንዳሉት ጥናት ባላደርግም በግምት ጣልያን የሰራው አንድያ የአቃቂ አስፓልት እሱ ብቻ ስለነበረ ይሆናል፡፡ አሁን ሁለት ሳይሆኑ በፊት፡፡ በነዋሪው አዲሱ አስፓልትና አሮጌው ተብለው ተሰይመዋል አስፓልቶቹ፡፡ ከተማ የተባለበት ሌላውን ምክንያት ስጠረጥር ደግሞ በርከት ብለው ካፌዎች፣ጠጅ ቤቶች፣ ማከፋፈያዎች እና መኪናዎች ስለሚገኙበት ሳይሆን አይቀርም ብያለህ፡፡ አትቀየሙኝ የሰፈር ልጆች፡፡ “ከተማ ነኝ ቃለአብ ካፌ ፊት ለፊት”፡፡ ወደመንደር ከገባችሁ ጋሪዎች በብዛት አሉ ታፔላ ቢኖራቸው ከቼንቶዎቹ በብዙ እጥፍ ይሻላሉ፡፡ እነሱም ከተማ አምሯቸው ወጣ ያሉ ቀን ታረጋቸው ይፈታል፡፡ ለጋሪዎቹና ሾፌሮቻቸው ምርጥ ቀን ታሕሳስ 12 ቀን ናት፡፡ ፃድቁ አባታችን አቡነ ሳሙኤል ስለሚነግሱ ባንዲራ በባንዲራ ሆነው 12 ሰው በአንድ ጋሪ ይጭናሉ፡፡ የዛን ቀን ፈረሶቹ ቢጎዱም ትርፍ ሰው በማጫን የሚከሳቸው ግን ማንም የለም፡፡

ግርምት ቁጥር 3

ቼንቶዎች ውስጥ

በነዚህ ቼንቶዎች መሳፈር ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ቢሆንም እነሱን አያሳጣን፡፡ ከጣጣዎቹ መካከል አንዱ ምንም ይሁኑ ምን በዕድሜም፣ በትምህርት ደረጃም ፣ በፆታም፣ በማዕረግም የሚያከብርዎት ረዳት ከመቶ አንድ ካገኙ መታደል ነው፡፡ ግን አያገኙም፡፡ በተራው ግን ከእግር ጥፍርዎ እስከራስ ጠጉርዎ ጫፍ ድረስ በግልምጫ፣ የመልስ ምት ከወረወሩ ደግም የአንደበት ዘለፋ ይድርስብዎታል፡፡ የስድቦቹን አይነት በዚህ ቦታ ላይ መጻፍ አላሻኝም፡፡ ምን ያደርጋል? በአቃቂ ቼንቶዎች ተሳፍረው ግን መሰደብ ይችላሉ ‘Live’፡፡ ለምን እንደሚሰደቡ ግን እኔ መንገር እችላለሁ፡፡ የመጀመርያው ስድብ ሊደርስብዎ የሚችለው ሃምሳ ብር ሰተው አርባ ስድስት ብር መልስ መጠየቅ ሲጀምሩ ነው፡፡ ሲቀበልዎ አንገብግቦ ነው፡፡ ሲመልስልዎ ግን ብርዎን ብቻም ሳይሆን ዝርዝር ስድብ መርቆ ነው፡፡ ሌላው ሊሰደቡበት የሚችሉበት ጉዳይ ደግሞ “ጠጋ ይበሉ” ተብለው “ወዴት ልጠጋ ከፊቴኮ ሰው አለ” ያሉ ጊዜ ነው፡፡ ሌላው የስድብ ድርሻ የሚከፈሎት ደግሞ “እባክህ ረፈደ ሠራተኞችና ተማሪዎች ነን ፈጠን አርገህ ንዳው” ያሉ ጊዜ ነው፡፡ የዛኔ መኪናው ሳይሆን የሚፈጥነው በርሶ ላይ የሚወነጨፈው ተወንጫፊ ስድብ ነው፡፡ እድለኛ ተሰዳቢ ከሆኑ ረዳቱ ብቻ ሳይሆን ሾፌሩም ድርሻ አለው፡፡ ምክንያቱም ፈጠን በል ማለትዎ በችሎታው መምጣትዎ ነውና፡፡
በቼንቶዎች ውስጥ ከረዳቶችና ሾፌሮች ውጭ ተሳፋሪውም እርስ በርሱ ይሰዳደባል ይጣላል ይጨቃጨቃል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ነው፡፡ ዋናዋናዎቹ 1ኛ. ገፋኸኝ ገፋሽኝ 2ኛ. መስኮት ክፈት ዝጋ 3ኛ. ወንበር ይዞ ለሰው ነው የያዝኩት አትቀመጡም ወዘተርፈ በሚሉት ምክንያቶች ነው፡፡ ሦስተኛው ምክንያት ከለገሃር ሲነሱ ይብስ የነበረ ሲሆን አሁን ሰልፍ በመጀመሩ በዚህ ጉዳይ የሚጣላ ብዙ የለም፡፡ እንጂማ ዋነኛው አደባዳቢ ጉዳይ ነበር፡፡ መኪና ውስጥ ለመግባት እንደባደባለን ከገባንም በኋላ እንደባደባለን፡፡ አቅመ ደካሞችን የሚያስታውሳቸው የለም፡፡ አሁን ለተራ አስከባሪዎቹ ምስጋና ይግባቸውና ገላግለውናል፡፡

ግርምት ቁጥር 4

ከአቃቂ እስክ ለገሃር

አሁን ከቼንቶዎቹ አሳብ ወጣ ልበልና በመንገድ ላይ የተገረምኩባቸውን ነገሮች በትንሹ ላካፍላችሁ፡፡ በዚህ ረጅም ጉዞ ሲጓዙ ከጎንዎ የሚያጫውትዎ ሰው ካልገጠምዎ መንገዱ አይግፋም በጣም ያሰለቻል፡፡ ስለዚህ በመስኮት ውጭ ውጭውን እያዩ ለመሄድ ይገደዳሉ፡፡   
በዚህ አሰልቺ ጉዞ ውስጥ ብዙ የሚገረሙባቸውን ነገሮች ይመለከታሉ፡፡ ከነዚህም መካከል የመንገዱ ሁኔታ ቀልቤን ይስበዋል፡፡ በተለይም ከቃሊቲ ቶታል እስከ ማረሚያ ቤት ያለው፡፡ ውበቱ እንዳይመስላችሁ ቀልቤን የሚስበው ማንገላታቱ ነው፡፡ “አስፓልት እዚህ ጋር ነበር” የሚል ጽሑፍ ካለተለጠፈበት በቀር የት ጋር እንደነበር ማወቅ ያዳግታል፡፡ ትራፊክ ፖሊሶች መሃል ጉድጓድ ውስጥ ቆመው መንገድ ሲያመላክቱ ይውላሉ፡፡ አንዳንዴም በደቦ ድንጋይ ሲደለድሉ አያቸዋለሁ፡፡ ሥራው የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም እነሱን ማድከም ግን ተገቢ ሆኖ አልታየኝም፡፡ ስለዚህ የመንገዶች ባለስልጣን ሊያስብበት ይገባል፡፡ ይህ መንገድ ለነፍሰ ጡሮች አዳጋች ነው፡፡ ሁሉም ቦታ ግን ተበላሽቷል ማለት እንዳልሆነ ተገንዘቡልኝ፡፡
በዚህ መንገድ ላይ ሌላው አስገራሚ ትዕይንት ፈረሶች ናቸው፡፡ ፈረሶቹ ጥንድ ጥንድ ሆነው መሃል መንገድ ላይ ይቆማሉ፡፡ የትራፊክ መጨናነቅም ይፈጥራሉ፡፡ እኔን ግን የገረመኝ ለምን ካለጠፋ ቦታ መሃል አስፓልት ላይ እንደሚቆሙ ነው፡፡ ብዙ ግዜ ራሴን ስጠይቅ ከቆየሁ በኋላ አንድ ቀን የሆነ ሰው እንዲህ ሲል ሰማሁት “እነዚህ ፈረሶች ለምን መሃል አስፓልት ላይ እንደሚቆሙ ታውቃላችሁ ለሁለት ነገር ነው አንደኛ ቁስላቸውን የሚበላውን ዝንብ በመኪናው ጭስና ነፋስ ለማባረር ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በመኪና ቢገጩ ባሌቤታቸው ከገጪው ካሳ ለመቀበል ነው፡፡” አስገራሚ ብልሃት ነው፡፡ እግረ መንገዴን ስለፈረሶቹ የታዘብኩትን ልንገራችሁ፡፡ አቃቂ ፈረሶች ውጪ ያድራሉ ሆኖም ግን ጅብ አይበላቸውም፡፡ ለምን? የሞተ ፈረስ ግን  ለሊቱን አይቆይም ተበልቶ ያድራል፡፡
ሌላው አስገራሚ ነገር ደግሞ ውሾች ናቸው፡፡ ከአቃቂ ተነስተው ሳሪስ አቦ ድረስ እስኪደርሱ ድረስ ካልታከቱ በቀር በየተወሰነ ርቀት ወደ ቆዳነት የተቀየሩ የውሻ ሬሳዎችን ይቆጥራሉ፡፡ ዋና ሳጅን አንድ ቀንም ስለነዚህ ውሾች ሞት ሲዘግቡ አልሰማሁም፡፡ ለነገሩ “አሳዳጊዎቻቸው እናሳድጋለን ብለው ከወገን ዘመዶቻቸው ለይተው ካመጧቸው ወዲህ እንደ ራሳቸው ውሾች ስለማያዩአቸው አስፓልት ብቻቸውን እንዲሻገሩ ስለሚያደርጉ ነው ብዙ ውሾች ተገጭተው የሚሞቱት” ብለው እንዲዘግቡ መጠበቅ የዋህነት ነው፡፡ የሰለጠነው ዓለም ቢሆን ኖሮ … ፈርዶብኝ ውሻ በጣም ስለምወድ ያሳዝኑኛል፡፡እርግጥ ነው ቻይና ከምትበላቸው መኪና ቢበላቸው ይሻላል፡፡

ግርምት ቁጥር 5

ጎተራ ማሳለጫ

ዘልዬ ማሳለጫው ላይ ለምን እንደወጣሁ ታውቃላችሁ? ሥራ እንዳይረፍድብኝ ከቼንቶው ወርጄ ታክሲ ውስጥ በመግባቴ በመሃል ያለውን መንግድ ሳልታዘብ በማለፌ ነው፡፡ ዕድሜ ለቻይና የሠራችውን መንገድ ደግማ እያፈረሰችው ነው፡፡ ማሳለጫውን አልወጣኝም፡፡ እሱን እያፈረሰው ያለው የሀገሬ ሾፌር ነው፡፡ ማሳለጫው ከተሠራ 100 ዓመት አለፈው አይደል? ከሰው ጋር ተከራክሬ  እሱ “ገና 2ኛ ዓመቱ ነው ከተመረቀ” አለኝ ላምነው አልፈለኩም 100 ዓመት ካልኩ አልኩ ነው በቃ፡፡ በጣም አርጅቷል፡፡ በቶሎ እንደቻይና ጫማ፡፡ ለካ ማሳለጫውም የቻይና ኑሯል፡፡
ማሳለጫው የብሄር ብሄረሰቦች አደባባይ መባሉን ሰምቼ ነበር፡፡ እኔም እንደዛው ነው የማምነው፡፡ ምክንያቱም የኦሎምፒክ አርማ በመሰለ የተሰናሰለ ብረት ክብ…ክብ ነገር ላይ የብሄር ብሄረሰቦችን የሚወክሉ ሰዎች ፎቶ ግራፍ ተለጥፎ ስለነበረ፡፡ አሁን ግን የለም፡፡ ካላመናችሁኝ ሂዱና እዩት፡፡ ብረቱ ላይ ልጆች ዥዋ ዥዌ ሲጫወቱበትና ፖሊሶች ቁጭ ብለውበት ትመለከታላችሁ፡፡ መንገዱ ሲሰራ ብዙ የተወራለት ነገር ነበር በዙሪያውና በውስጡ ይኖራል የተባለ ግን ምንም የለም፡፡ ቃላችንን ለምን አንጠብቅም? ሁል ጊዜ በዘመቻና በመፈክር ብቻ ለምን እናምናለን? ቅዳሜና ዕሁድ የጦፈ እግር ኳስ ጨዋታ ይካሄድበታል፡፡ ኳስ በሚጫወቱት መፍረድ አይቻልም፡፡ የት ሄደው ይጫወቱ? ከአምስት እስከ ስድስት ዓመታት በፊት እግር ኳስ ሜዳዎች በገፍ እንዳልነበሩ አሁን አንዳቸውንም ማግኘት አይቻልም፡፡ በጭራሽ፡፡ በምትካቸው ባለ ሦስት ፎቅ ቤቶች ተሰርተውባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢንዱስትሪ መንደር የተገነባባቸውም አሉ፡፡ እነዚህ ሜዳዎች በርካታ እስፖርተኞችን ያፈሩ ነበሩ፡፡ ከትንሽ ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ ሃገራችን በእግርኳሱ ሳይሆን በፑልና ከረንቦላ ለተከታታይ 10 ዓመታት የዓለም ዋንጫን ያለጥርጥር ማንሳት እንደምትችል እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ የወጣት ማዕከል ተብለው እግርኳስ ሜዳዎች ላይ የተገነቡት ፑልና ሹሌ ነው የሚሳለጥባቸው፡፡ ትኩረት ቢደረግበት ያዋጣል፡፡
የተነሳሁበትን ረሳሁት መሰል? ወደ ቀደመው… ይልቅስ ማሳለጫው የሚያሳልጠው መኪና ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ብዙ የሚያሳልጠው ጉድ አለው፡፡ ምን ምን አትሉኝም ሃብታም ጎዳና ተዳዳሪዎች እንቅልፋቸውን ያሳልጡበታል፡፡ መሄጃ ያጡ አልያም ቦታው ማርኳቸው ባላውቅም ፍቅረኞች ሁለቱ እንደ አንድ ሆነው ፍቅራቸውን ያሳልጡበታል፡፡ ከነሱ ትንሽ ፈቅ ብሎ ደግሞ ሎተሪ አዝዋሪና ሌላውም ላብ አደር እዛው አደሮችንም ጨምሮ እዳሪያቸውን ያሳልጡበታል፡፡ የብሄር ብሄረሰቦች አደባባይ ውስጥ፡፡
ሌላው ደግሞ ምን መሰላችሁ የሚሳለጠው በማሳለጫው የዓመት በአል ሰሞን በጎችና ከብቶች እንደጉድ ይሳለጡበታል፡፡ ጠያቂም የላችው፡፡ ለምን የሚል የለም፡፡ የበግ ዋጋ የሚጠይቅ ግን ሞልቷል፡፡ ያውም መኪና አቁሞ፡፡ ይሄኔ ያ ሰው ማን ያውቃል በየሚድያው አረንጓዴና ምቹ ምናምን እያለ የሚነተርከን ይሆናል፡፡ ማሳለጫውን ተሻግሬያለሁ አበቃሁ፡፡  
ጥቅምት 22 ቀን 2005 ዓ.ም

No comments:

Post a Comment