ባለፉት ተከታታይ ቀናት አመሻሹን በዘነበው ዝናብ ምክንያት የአዲስ
አበባን መንገዶች ውሃ ሞልቷቸው ነበር፡፡ የከተማዋ በየቦታው መቆፈርና መታረስ የትራንስፖርት ችግር ከማስከተሉም ባሻገር መንገገዶቿም
ወንዝ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል፡፡ በተለይ የካቲት 16 የዘነበው ኃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ የመላው አፍሪካ ሃገራት የወንዝ
ኤግዚብሽን በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ እየተካሄደ ያለ አስመስሎታል፡፡
በውሃ የተጥለቀለቁት መንገዶች ፈርሰው እየተገነቡ ያሉት ብቻ
ቢሆኑ አያስገርምም፡፡ ይልቅስ አዳዲሶቹና ዘመናዊ የተባሉትም መንገዶች ወንዝ የሆኑ ይመስላል፡፡ በየጊዜው የሚለፈፍ ቢሆንም አሁንም
የከተማዋን የፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓት አንኳር ጥያቄ ውስጥ የሚዶል ነው፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች በሙሉ በሚያሰኝ አኳኋን የታሸገ
ውሃ መያዣ ላስቲክና የጫት ትራፊ ሞልቷቸዋል፡፡ ተጠቃሚውም አጥፊ ሰሪውም ግድ የለሽ፡፡ በዛ ላይ አብዛኞቹ መንገዶች በመታጠራቸው
ጠበዋል፡፡ መጥበባቸው ብቻ አይደለም ጉዳቱ ሰዎች እንደ እንቁላል እየተነሱ ይፈርጡበታል፡፡ ድሮ ሰው ሲወድቅ “አከሌ መሬት ገዛ”
ተብሎ ይቀለድ ነበር፡፡ አሁንስ? ‘ሊዙን’ ማን ይችለዋል? ባይወደቅ ቢቀርስ!
እነዚህ እየተገነቡ ያሉት መንገዶች ለሁለት ጥቅም ታስበው ተሰርተው
እንደሆን ለሰፊው ሕዝብ ቢገለፅ ውብ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተነገረውም፡፡ ቢነገረው አቅም ያለው አነስተኛ ጀልባ ይገዛል አልያም
ይከራያል፡፡ የሌለው ደግሞ ቦት ጫማ ለመግዛት አያንስም ነበር፡፡ በቆዳ በሸራና በስኒከር ጫማዎች የአዲስ አበባን መንገዶች መጓዝ
ጦሱ ላፍንጫ ነው፡፡ አሁን የአዲስ አበባን መንገዶች እንደወንዝ እንጂ እንደሌላ ማሰብ እንዴት ይቻላል? በትልልቅ አለቶችና አሸዋ
የተሞላን መንገድ ወንዝ እንጂ ምን ይሉታል? በተለይ እንደ ገበጣ መጫዎቻ የተፈነካከተውን ከቃሊቲ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ አንስቶ
እስከ ቃሊቲ ቶታል ያለውን አስፓልት መሳይ ያየ መንገዶቻችን እንዴት ባለ ጥራት እንደሚገነቡ ያስተውላል፡፡
በነገራችን ላይ አልሰማሁ ይሆናል እንጂ ባለፈው ምርጫ ቅስቀሳ
ወቅት ከተመራጮች አንዱ ወይ ሁለቱ እንዲህ ብለው ከነበረስ ‹‹የአዲስ አበባን ሕዝብ የወንዝ
ፍላጎት ለሟሟላት መንገዶች ሁሉ ወንዝ እንዲሆኑ የወንዞቹን ቁጥር በእጥፍ እናሳድጋለን፡፡ ለዚህም ስኬት እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንሰራበት ሂደት ነው ያለው፡፡›› ተሳክቶላቸዋል፡፡ ድጋሚ እንመርጣችኋለን
እኛ የወንዝ አምሮታችን የወጣልን አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፡፡
