ሁለተኛው ትእዛዝ
‹‹የእግዚአብሔርን
የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።›› ዘጸ 20፡7፡፡ ይህ ትእዛዝ የሚያተኩረው በስመ እግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ስም ቅዱስ፣ ታላቅና
ድንቅ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ስም በልማድ ዝም ብለን የምንጠራው ስም አይደለም፡፡ ‹‹ዘይትህ መልካም መዓዛ አለው ስምህ እንደሚፈስስ ዘይት ነው ስለዚህ ደናግል
ወደዱህ።›› መኃ 1፡3 በማለት ጠቢቡ ሰሎሞን እንደታናገረው ስሙን የምንጠራው በጸሎተ እጣን እንደምናደርገው በአክብሮትና በተዋቡ
ቃላት ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ‹‹ብርቱ የሆነ
እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤ ስሙም ቅዱስ ነው።›› ሉቃ 1፡49፡፡ በማለት ነግራናለች፡፡ ልበ አምላክ ዳዊትም በመዝሙሩ
‹‹ስሙ የተቀደሰና የተፈራ ነው›› መዝ 110፡9 ብሎናል፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችንም ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማረው ጸሎት
‹‹ስምህ ይቀደስ›› ማቴ 6፡9፡፡ በማለት ያስተማረንም የስሙን ቅድስና ልብ እንድል ነው፡፡ ስለዚህ ስሙን ስንጠራ በመፍራትና በመንቀጥቀጥ
ለቅዱስ ስሙ አክብሮት በመስጠት መሆን አለበት፡፡ የሰማይ ካህናት ሱራፌል ‹‹ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር
ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች፡፡›› እያሉ ቅዱስ ስሙን ያመሰግናሉ፡፡ ይህም ቅዱስ ስም ሱራፌል በመንቀጥቀጥና በመፍራት የዘመሩለት፣ ቤቱ
በጢስ የተሞላበትና የተናወጠበት… ነው፡፡ ኢሳ 6፡1-5፡፡
አርባዕቱ እንስሳና ሃያ አራቱ ካህናተ ሰማይ ለዚህ ስም ‹‹አራቱም እንስሶች እያንዳንዳቸው ስድስት ክንፎች
አሉአቸው፥ በዙሪያቸውና በውስጣቸውም ዓይኖች ሞልተውባቸዋል፤ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ ቅዱስ፥ የነበረውና ያለ የሚመጣውም ሁሉንም የሚገዛ
ጌታ አምላክ እያሉ ቀንና ሌሊት አያርፉም። እንስሶቹም በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ከዘላለምም እስከ ዘላለም በሕይወት ለሚኖረው ለእርሱ
ክብርና ውዳሴ ምስጋናም በሰጡት ጊዜ፥ ሀያ አራቱ ሽማግሌዎች በዙፋን ላይ በተቀመጠው ፊት ወድቀው፥ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሕይወት
ለሚኖረው እየሰገዱ። ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም
ልትቀበል ይገባሃል እያሉ በዙፋኑ ፊት አክሊላቸውን ያኖራሉ።›› ራእ 4፡8-10፡፡ በማለት ክብር እንደሚሰጡት ተጽፎልናል፡፡ ነቢዩ ሚልክያስም ‹‹ከፀሐይ መውጫ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ስሜ በአሕዛብ
ዘንድ ታላቅ ይሆናልና በየስፍራውም ለስሜ ዕጣን ያጥናሉ፡፡›› ሚል 1፡11፣ ነቢዩ ኤርምያስም ‹‹አቤቱ፥ እንደ አንተ ያለ የለም
አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው።›› ኤር 10፡6፣‹‹ተቤዢአቸው ብርቱ ነው፥ ስሙም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው፡፡››
ኤር 50፡36፣ ኢያሱ ወልደ ነዌም ‹‹ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው?›› ኢያ 7፡9፣ ልበ አምላክ ዳዊትም ‹‹የሠራዊት
ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል አምላክ ነው ይባል ዘንድ ስምህ ለዘላለም ታላቅ ይሁን፡፡›› ካል ሳሙ 7፡26፡፡ በማለት ስሙ ቅዱስ
እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
‹‹የእግዚአብሔርን የአምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ከበደል አያነጻውምና።››
ዘጸ 20፡7፡፡ የሚለው ትእዛዝ ዓላማ ቅዱሳን መላእክትና የእግዚአብሔር ወዳጆች የሆኑ የሰው ወገኖች በመፍራትና በመንቀጥቀጥ የሚጠሩትን
እንዲሁም የሚገዙለትን ቅዱስ ስም እኛም በክብር በትሕትና እንድንጠራው ማድረግ ነው፡፡ የአምላካችን የእግዚአብሔር ስሙ ድንቅ ተአምራትን
ያደርጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በቤተ መቅደስ ደጅ ያገኙትን የታመመ ሰው ‹‹ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤
በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው።›› የሐዋ 3፡6፡፡ በዚህ ቅዱስ ስምም ሽባው ሰው ተፈውሶ ወደ ቤተ መቅደስ
ገብቶ አመስግኗል፡፡ ሐዋርያቱም በአይሁድ በተጠየቁ ጊዜ ይህን ድንቅ ነገር ያደረጉት በእግዚአብሔር ስም እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የሐዋ 4፡7-8፡፡ ሐዋርያቱ ‹‹አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ
ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።›› የሐዋ 4፡29-30፡፡ በማለትም በጸሎት
ጠይቀዋል፡፡ ይህም ሆኖ በስሙም ምትሐታዊ ተአምራት የሚያደርጉ እንዳሉና
እንደዚህ ያሉት በፍርድ ቀንም የሚፈረድባቸውም እንደሆኑ ማስተዋልም ያስፈልጋል፡፡ ‹‹በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥
በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን
ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።›› ማቴ 7፡22-23፡፡ የእግዚአብሔርን ስም
አጋንንት ይፈሩታል ይደነግጣሉም ‹‹ሰብዓውም በደስታ ተመልሰው። ጌታ ሆይ፥ አጋንንት ስንኳ በስምህ ተገዝተውልናል አሉት።›› ሉቃ
10፡17፡፡ እንዳሉ፡፡ ጌታችንም ‹‹ያመኑትንም እነዚህ ምልክቶች
ይከተሉአቸዋል፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ፤ እባቦችን ይይዛሉ፡፡ ማር 16፡17፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እየጠነቆለች ገንዘብ ታስገባ የነበረችውን ጋኔን ያደረባት ሴት
‹‹ይህንም እጅግ ቀን አደረገች። ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን። ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ
አለው፤ በዚያም ሰዓት ወጣ።›› የሐዋ 16፡18፡፡ ተብሎ እንደተጻፈልን በቅዱስ ስሙ አጋንንት ወጥተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን
በተቀደሱ የጠበል ስፍራዎች ሁሉ የምንመለከተው ይኸው ነው፡፡
የእግዚአብሔር የአምላካችን ስም በችግር ጊዜ የምንመካበት መጠጊያችን ነው፡፡ ጥበበኛው ሰሎሞን ‹‹የእግዚአብሔር
ስም የጸና ግምብ ነው ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል።›› ምሳ 18፡10፣ ልበ አምላክ ዳዊትም ‹‹አሕዛብ ሁሉ ከበቡኝ፥
በእግዚአብሔርም ስም አሸነፍኋቸው፡፡›› መዝ 117፡10፣ ‹‹በአንተ ጠላቶቻችንን እንወጋቸዋለን፥ በስምህም በላያችን የቆሙትን እናዋርዳቸዋለን።››
መዝ 43፡5፣ ‹‹አቤቱ በስምህ አድነኝ፡፡›› መዝ 53፡1 በማለት የተናገሩት የእግዚአብሔር ስም ከመከራና ከጭንቅ የሚያድን መሆኑን
ለማስረዳት ነው፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር በኢሳ 50፡10 ‹‹በእግዚአብሔር
ስም የሚታመን፥ በአምላኩም የሚደገፍ ማን ነው?›› በማለት እንደጠየቀው በስሙ እንድንታመን ይሻል፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ስም እንጂ በዚህ ዓለም ባለ ከንቱ ነገር እንዳይታመን ይገባዋል፡፡
‹‹በመካከልሽም የዋህና ትሑት ሕዝብን አስቀራለሁ በእግዚአብሔርም ስም ይታመናሉ።›› ሶፎ 3፡12፣ ‹‹ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ
ታደርገዋለች፥ረዳታችንና መጠጊያችን እርሱ ነውና። ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና።›› መዝ 32፡20-21፡፡ እንደተባልን፡፡
የእግዚአብሔር የአምላካችን ስም ጸጋው የሚሰጥበት ስም ነው፡፡ በቤተ
ክርስቲያናችን ምስጢራት ሁሉ የሚፈጸሙት በእግዚአብሔር ስም ነው፡፡ ማቴ 28፡19 ጥምቀት፣ ያዕ 5፡14 እንዲል፣ … ካህናትም ሕዝቡን
የምንባርከው በእግዚአብሔር ስም ነው፡፡ ዘኁ 6፡24-26፡፡ የእግዚአብሔር የአምላካችን ስም ክብር የሚገባው ስም ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ‹‹<<አምላክህ እግዚአብሔር>> የተባለውን
የተመሰገነውንና የተፈራውን ስም ባትፈራ..›› ዘዳግ 28፡58 በማለት ያስጠነቀቀን ስሙ ክብር የሚገባው መሆኑን ለማሳሰብ ነው፡፡
ስሙን የሚፈሩና የሚያከብሩትም ‹‹ስምህንም ለሚፈሩት ለታናናሾችና ለታላላቆችም ዋጋቸውን ትሰጥ ዘንድ›› ራእ 11፡18 እንደተባለው
ዋጋ ያገኛሉ፡፡ እኛም ‹‹የተቀደሰ ስምህን ኃጢአት ባረከሰው አንደበታችን
እንጠራው ዘንድ የሚገባን አይደለም›› በማለት ከልበ አምላክ ዳዊት ጋር ‹‹በአንድነት ስሙን ከፍ ከፍ ልናደርግ›› ልንጠራው ይገባናል፡፡
መዝ 33፡3፡፡
የእግዚአብሔር የአምላካችን ስም ክብር የሚገባው ስም ነው…
የእግዚአብሔርን ስም በሆነው ባልሆነው መጥራት አይገባም፡፡ ስሙን ስንጸልይ፣ ስለ ቸርነት ሥራው ስናመሰግን…
ብቻ በክብር የምንጠራ መሆን ይገባናል፡፡ ‹‹በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፡፡›› መዝ 104፡3፣ ‹‹በልዑል እግዚአብሔር ስም እዘምራለሁ፡፡››
መዝ 7፡17 የተባለው የሚያሳስበንም ይህንኑ ነው፡፡ የእግዚአብሔርን
ስም እውነተኛ አክብሮት ሳይኖር በልማድ ብቻ መጥራት አልተፈቀደም፡፡ ‹‹የመበለቶችን ቤት የሚበሉ ጸሎታቸውንም በማስረዘም የሚያመካኙ፥
እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ አለ።›› ሉቃ 20፡47፡፡ የተባለላቸው ፈሪሳውያን የእግዚአብሔር ፍቅር በልቦናቸው ሳይኖር ለሰው
ፊት ለመታየት ብቻ ይሠሩት ከነበረው የተነሳ ነው፡፡ በምናስተምርበትም
ጊዜ ‹‹ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው።›› የሐዋ 9፡16፣ ‹‹ታግሠህማል፥ ስለ ስሜም
ብለህ ጸንተህ አልደከምህም።›› ራእ 2፡13፡፡ ‹‹እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቈጠሩ ከሸንጎው ፊት
ደስ እያላቸው ወጡ፡፡›› የሐዋ 5፡41 እንደተጻፈልን ስለስሙ መነቀፍን በጸጋ በመቀበልማገልገል ይኖርብናል፡፡
ስሙን በከንቱ መጥራት
በደለኛ ሰው የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ ይጠራል፡፡ በፌዝ፣ ወይም በሌሎች ከንቱ ነገሮችም ውስጥ ሳይቀር ስሙን
በከንቱ ይጠሩታል፡፡ በስሙ መማል ጌታችን መሐላን ‹‹እኔ ግን እላችኋለሁ።
ከቶ አትማሉ … ነገር ግን ቃላችሁ አዎን አዎን ወይም አይደለም አይደለም ይሁን›› ማቴ 5፡34-37፡፡ ፈጽሞ ከልክሎናል፡፡ በብሉይ
እውነት ለሆነ ነገር መሐላ ተፈቅዶ ነበር፡፡ ‹‹በስሜም በሐሰት አትማሉ፥ የአምላካችሁንም ስም አታርክሱ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።››
ዘሌዋ 19፡12፡፡ ‹‹በዚያን ጊዜ ከግብፅ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ። አምላክህን እግዚአብሔርን
ፍራ እርሱንም አምልክ በስሙም ማል።›› ዘዳግ 6፡12-13፡፡ ‹‹አምላክህን እግዚአብሔርን ፍራ፥ እርሱንም አምልክ ከእርሱም ተጣበቅ፥
በስሙም ማል።›› ዘዳግ 10፡20 በማለት በሌሎች አማልክት ስም እንዳንምል እውነት ለሆነው በስሙ እንድንምል ፈቅዶ ነበር፡፡ ይህም እግዚአብሔር በኢያሱ ‹‹በእናንተ መካከል ወደ ቀሩት ወደ እነዚህ አሕዛብ
አትግቡ የአማልክቶቻቸውንም ስም አትጥሩ፥ አትማሉባቸውም፥ አታምልኩአቸውም፥ አትስገዱላቸውም፡፡›› ኢያ 23፡7 በተናገረው ግልጥ
ሆኖአል፡፡ በተጨማሪም አምላካችን እግዚአብሔር በኤር 12፡16
‹‹በበኣል ይምሉ ዘንድ ሕዝቤን እንዳስተማሩ በስሜ። ሕያው እግዚአብሔርን! ብለው ይምሉ ዘንድ የሕዝቤን መንገድ በትጋት ቢማሩ፥
በዚያን ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ።›› ብሎናል፡፡ ኤር 5፡7፣ ኢሳ 48፡1፣ መዝ 62፡11፣ ኢሳ 45፡23 በማለት ባዕዳን
አማልክትን በሚያመልኩት መካከል ስሙ መታወቂያ ይሆናቸው ዘንድ በስሙ ይምሉ ዘንድ በብሉይ ዘመን ፈቅዶ ነበር፡፡ የባዕዳን አማልክት
አማልክት ከተወገደ በኋላ ግን በስሙ መማል ስላላስፈለገ ‹‹ፈጽማችሁ አትማሉ›› ብሎ አዘዘን፡፡ ማቴ 5፡23፡፡ ይህም ስለስሙ ክብር
እንዲሰጡ ከንቱ በሆነው ነገር ሁሉ ስሙን እንዳይጠሩ ነው፡፡ ፈሪሳውያን
እየበደሉም ቢሆን በድፍረት ስሙን የሚጠሩበት ሥርዓት ሰርተው ነበር፡፡ ማቴ 23፡16-22፣ ቀዳ ሳሙ 25፡30-33፡፡ ስለዚህ ጌታችን እየማሉ እገድለዋለሁ፣ አስጠነቁልበታለሁ፣ አጠፋዋለሁ፣ እያሉ
መጥፎም ለመሥራት የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ በማንሳት የሚምሉ ስላሉ አትማሉ ብሎ ለሐዲስ ዘመን ክርስቲያኖች ትእዛዙን ሰጠን፡፡
ቤተ ክርስቲያን ላለመሄድ፣ ንስሐ ላለመግባት፣… በሐሰት መጽሐፍ ቅዱስ
ጨብጠው የሚምሉም ስላሉ አትማሉ አለን፡፡ ክርስቲያኖች ቃሉን እንዲያከብሩት
በምንናገርበት ጊዜ መሐላን በማብዛት ሳይሆን ማንም ሰው ቢሆን ባያምነንም እንኳበቀጥታ እውነት የሆነውን እንናገር፡፡ እንድንምል
ቢጠይቀን እንኩዋ የተናገርሁት እውነት ነው ማመንም ሆነ አለማመን ግን መብትህ ወይም ነጻነትህ ነው እንበለው፡፡ በሰው ፊት ታማኞች
እስከሆንና ሐሰትን ተናግረሃል ብሎ ማንም ሊከሰን እስካልቻለ ድረስ ሳንምልም ሰዎች ሊያምኑን ይችላሉ፡፡ ሰዎችም እውነት እስከተናገርን
ድረስ ስለተናገርነው የእግዚአብሔር እውነት ማስረጃ እንዲጠይቁን አንተዋቸው፡፡ የእግዚአብሔር ስም በበርካታ ሰዎች አንደበት ውስጥ ቀሎ ይታያል… ሌሎችን ለመዝለፍ፣
ለተረት፣ ለፌዝ፣ ለንዴታችን፣ ለጭቅጭቃችን ስሙን በከንቱ የምናነሳ ካለን ምን ያህል ከንቱ እንደሆነ ልብ እንበል፡፡ ስሙን ስንጠራ ኢየሱስ ብቻ ብለን አቅለን እንዳንጠራ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማረችን
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብለን በአክብርት እንጠራ ዘንድ አስጠነቀቀን፡፡
በዚህ ሕግ ስሙን መስደብ ወይም ማርከስ ተከልክሏል
‹‹የእግዚአብሔርንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል ማኅበሩም ሁሉ ይውገሩት መጻተኛ ወይም የአገር ልጅ ቢሆን፥
የእግዚአብሔርን ስም በሰደበ ጊዜ ይገደል።›› ዘሌዋ 24፡16፡፡ ‹‹ወደ መጡባቸውም ወደ አሕዛብ በመጡ ጊዜ፥ ሰዎች እነርሱን፦ ከምድሩ የወጡ
የእግዚአብሔር ሕዝብ እነዚህ ናቸው ሲሉአቸው ቅዱስ ስሜን አረከሱ። እኔ ግን የእስራኤል ቤት በመጡባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሱት
ስለ ቅዱስ ስሜ ስል ራራሁላቸው። ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤል ቤት ሆይ፥
በመጣችሁባቸው በአሕዛብ መካከል ስላረከሳችሁት ስለ ቅዱስ ስሜ ነው እንጂ ስለ እናንተ የምሠራ አይደለሁም።›› ሕዝ 36፡20-22፡፡
‹‹እንዲህም አለኝ፦ ይህ በምድር ፊት ሁሉ ላይ የሚወጣው እርግማን
ነው የሚሰርቅ ሁሉ በእርሱ ላይ በዚህ በኩል እንደ ተጻፈው ሁሉ ይጠፋል፥ በሐሰት የሚምልም ሁሉ በእርሱ ላይ በዚያ በኩል እንደ
ተጻፈው ሁሉ ይጠፋል። እኔ አስወጣዋለሁ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ ወደ ሚሰርቀውም ቤት፥ በሐሰትም በስሜ ወደሚምለው ቤት
ይገባል በቤቱም ውስጥ ይኖራል፥ እርሱንም፥ እንጨቱንና ድንጋዩን፥ ይበላል። ከእኔም ጋር ይነጋገር የነበረው መልአክ ወጥቶ። ዓይኖችህን
አንሣ፥ ይህችም የምትወጣው ምን እንደ ሆነች እይ አለኝ።›› ዘካ 5፡3-4፡፡ ‹‹ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ ባትሰሙ፥ በልባችሁም ባታደርጉት፥ ይላል የሠራዊት
ጌታ እግዚአብሔር፥ እርግማን እሰድድባችኋለሁ፥ በረከታችሁንም እረግማታለሁ አሁንም በልባችሁ አላደረጋችሁትምና እኔ ረግሜአታለሁ።››
ሚል 2፡22፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ስሙን በከንቱ የሚጠራውን ሰይጠይቀው አይተወውምና ዘወትር የእግዚአብሔርን
ስም ዘወትር እናመስግን እንቀድስ፡፡
ይቆየን

No comments:
Post a Comment