ነገረ ማርያም/ክፍል አንድ/
«አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ፤» መኃ 4:7
የትንቢተ ነቢያት ማረፊያ ፡-የስብከተ ሐዋርያት መነሻ.የሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምሥጢር ነገረ ማርያም ነው፡፡ ያለ ነገረ ማርያም ነገረ ክርስቶስን መናገር አይቻልም፡፡ በክርስትና ሃይማኖት ታሪክ የተነሡ አያሌ መናፍቃን የመጀመሪያ ችግራቸው የነገረ ማርያምን አማናዊ ትምህርት መቀበል ነበር ፡፡ ያም ችግራቸው ክርስቶስን በትክክል እንዳያምኑት አድርጓቸዋል፡፡ በነገረ ማርያም ላይ የተጣራ ትምህርትና እምነት ቢኖራቸው ኖሮ ለኑፋቄ አይጋለጡም ነበር ፡፡ ንስጥሮስ፡- «አምላክ ወልደ አምላክ» ብሎ በክርስቶስ ለማመን የተሳነው « ወላዲተ አምላክ . ወላዲተ ቃል. እመ እግዚአብሔር » ብሎ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ለማመን በመቸገሩ ነበር፡፡