ትዝታ በየሁሉም
ሰው ልብና ሕሊና ውስጥ በአጭሩም በረዥሙም በቀጭኑም በወፍራሙም ብቻ በየትኛውም ሁናቴ ቦታ የለውም ማለት አይቻልም፡፡ ትዝታን በዘፈን፣ትዝታን
በግጥም፣ትዝታን በንግግር እንዲሁም ትዝታን በማብሰልሰል ማስታወስ የሕይወታችን መቆዘምያ መንገዶች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች
ትዝታዎቻቸውን ሲያወጉ መስማት በራሱ አንዳች ደስታን ይፈጥራል፡፡ በተለይም ዕድሜ ጠገብ የሆኑ አረጋውያን፡፡ በእውነት የተደረጉ
ሳይሆኑ በተለያዩ የተረት መጻሕፍት እንደምናነበው ዓይነት ይሆኑብናል፡፡ ግን እውነቶች ናቸው የተኖሩ፡፡ ለምሳሌ “በ25ሳንቲም ክተፎ
በላን” ፣ ”በ15 ሳንቲም በአውቶቡስ ደርሶ መልስ እንጓዝ ነበር፡፡ አንድ ጉዞ ብቻ የሚጓዝ ሰው በቀሪው ማስቲካና ከረሜላ መለወጥ ይችል ነበር” ፣ “1ኪሎ ጤፍ በ20 ሳንቲም ገዝተናል” እነዚህ እውነታዎች
ነገር ግን ትዝታዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሃገራችን የተኖሩ ያልተረሱ ትዝታዎች፡፡ እኔ “ምን ትዝታ አልኝ?” ብዬ ራሴን ብጠይቅ
ምንም፡፡ ምክንያቱም አኗኗሬ በጥንቃቄና በፍርሃት በሚኖርበት ጊዜ በመሆኑ፡፡ እድለቢስ ነኝ ልበል?
የሆኖ ሆኖ
ዛሬ ለመጻፍ የተነሳሁት በ facebook ገጼ ላይ በተደጋጋሚ ጓደኞቼ post እያደረጉልኝ
የተመለከትኩት ፎቶ ግራፍ ነው፡፡ ይህ ፎቶ ግራፍ የሰው ወይም የእንስሳ አልያም የሌላ ሥነ ፍጥረት እነዳይመስላችሁ የደብተር እንጂ፡፡
ደብተሩ ላይ ሁለት ወንድና ሴት ተማሪዎች ቦርሳ አንግተው ከኋላቸው የት/ቤት መለያ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ እና የመማርያ ክፍሎች
ይታዩበታል፡፡ ታድያ ሁሉም ጓደኞቼ post ሲያደርጉልኝ ተመሳሳይ
ጽሑፍ አለው፡፡ ከራስጌው ወይም ከግርጌው “በዚህ ደብተር ተምረው ያውቃሉ?” ይላል፡፡ ነገር ግን እስካሁን like’ን ከመጫን በቀር ምንም ምን ሃሳብ አልሰጠሁበትም፡፡ ለምን?
እንጃ ብቻ፡፡ ቁንጥር ብትሆንም ትዝታ አለችኝ፡፡ ከደብተሩ በስተጀርባ፡፡
