ኢትዮጵያዊ ነኝ ኢትዮጵያ ውስጥ የምኖር፡፡ ከነሐሴ
14/2004 ዓ.ም ወደዚህ እያየሁትና እየሰማሁት ያለሁት ነገር ራሴን እንድጠራጠር አድርጎኛን፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የክቡር ጠቅላይ
ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዜና እረፍት ከተነገረባት ሰዓት ጀምሮ ያለሁባት ኢትዮጵያ እሷ ናት ወይስ ሌላ? ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊስ
ቢሆኑ ሁለት ነበሩ እንዴ? እንድል አድርጎኛል፡፡ ሲያዝንና ሲያለቅስ የማየው ይህ ብሶተኛ ሕዝብ ከሌላኛዋ ኢትዮጵያ በሌላው ጠቅላይ
ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከምትመራው የመጣ ሳይሆን አይቀርም የሚል ጭምጭምታ ሽው ብሎኛል፡፡ ካደገችውና ዜጎቿ በነፃነት ከሚወጡባት
ከሚገቡባት፣ሸመታው ከረከሰባት፣የመብራት ኃይል ከማይቆራረጥባት፣የተጠበሰ ግማሽ በቆሎ እንደሚያማርረው ሕዝበ-ኢትዮጵያ በ3ብር ሳይሆን
በ20ሳንቲም ከሚገዛባትና እያማረው ምራቁን ከማይውጥባት፣ 1ኪሎ ሥጋ በ100ብር ሳይሆን በ20ብር ከሚቆረጥባት፣1ኩንታል ጤፍ
1600ብር ካልደረሰባት፣ ደሞዙ ከበቂ በላይ የሚያኖረውና የለውጥ አርበኛ ሕዝብ ከሚኖርባት ወዘተ… የመጣነው ለማለት የስደፍራል፡፡
ምክንያቱም ከነዚህ ዜጎች የሚወርደው የእንባ ዘለላ የሚያረጋግጠው እውነት ይህን ስለሆነ፡፡
እነዚህ ዜጎች የሚኖሩባት ኢትዮጵያ በትራንስፖርቱ ረገድ በፈጣን
ባቡሮችና ምቹ አውቶቡሶች ተንፈላሰው የሚማላለሱባት እንጂ በግፊያና በድብድብ የሚንገላቱባት ያቺ ኢትዮጵያ እንዳልሆነች እንባቸው
ያቃጥርባቸዋል፡፡ እነኛ ምስኪን መጠጊያ የሌላቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች በክቡር ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በሚመራው መንግስት የተነሳ ከዝናብና
ፀሐይ እንዲሁም ነፋስ ጋር ታግለው ድህነትን ታሪክ ጎዳና ተዳዳሪነትን ምቾት ካደረጉባት ሀገረ ኢትዮጵያ የመጡ እንጂ እኔ ከምኖርባት
ኢትዮጵያ እንዳልሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም የለበሱት ድሪቶ እንደተመቻቸው እንጂ እንደተቸገሩ የሚያሳይ አይደለማ፡፡
“በእውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ
ይችላልን?” የሚለው ቅዱስ ቃል የተነገረላቸው እኚህ ሕዝቦች የትኞቹ ናቸው? እነዚህ እንደማይሆኑ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እንዲህ እንደ
እስስት የሚለዋወጡትማ ይህ የትንቢት ቃል የተነገረላቸው በፍፁም ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ይልቅስ “ሆዳቸው አምላካቸው…” የተባለላቸው
ይሆናሉ እንጂ፡፡ በአንድ አፋቸው የሚመርቁ በአንድ አፋቸው የሚራገሙ ኢትዮጵያውያን የሉማ፡፡ ትናንት ከትናንት ወድያ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና
መንግስታቸውን መሬቴን ቀሙኝ፣ ኑሮዉን አናሩብኝ፣ እንደፈለኩ እንዳልናገር አፈኑኝ ሲል እንዳልነበር አሁን ምናግኝቶ ነው የደም እንባ
የሚያለቅሰው? እንኳን የቆመ ሙትም ይታዘባልና እባካችሁ አንሸዋወድ፡፡ ይህን ሕዝብ ማነው አቋሙን የነጠቀው? ደፋርና እውነተኛ ነበረ
የዛሬን አያድርገውና፡፡ በሌላ በኩል መጭውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሊያሳቅቁ
የሚችሉ ለምሳሌ “እሳቸው የሚተኩ መሪ አይደሉም” የሚሉ ጉንጭ አልፋ ንግግሮች ባይነገሩ እንመርጣለን፡፡ ከሆነማ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር
ምን ያስፈልገናል? እሳቸው “እንዲህ ነበሩ”፣“ይህን ወጥነዋል”፣“ይህን ተናግረዋል” በሚሉት ግዘፍ በሌላቸው ነገሮች መመራቱ ይበቃናል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ማዘን ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም ከልክ ያለፈ
ሲሆን የሚያስተዛዝብ ይሆናልና መጠን ቢበጅለት መልካም ነው፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቸቸው መፅናናትን እግዚአብሔር ያድል፡፡
