Monday, December 10, 2012

‹‹አትስረቅ።›› ዘጸ 20፡15፣ ዘዳግ 5፡19፡፡


ሰባተኛ ትእዛዝ
‹‹አትስረቅ።›› ዘጸ 2015 ዘዳግ 519፡፡
 ‹‹ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።›› ቀዳ ቆሮ 610፡፡

ሌብነት ምንድር ነው? የምንሰርቀውስ ከማን ነው?

ሌብነት የአንዱን ሰው ንብረት መካፈል ማለት አይደለም፡፡ ‹‹በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል አለፈ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተራቡና እሸት ይቀጥፉ ይበሉም ጀመር። ፈሪሳውያንም አይተው። እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ አሉት።›› ማቴ 121-2፡፡ እንዳለው ደቀ መዛሙርቱን ጌታችን ሲገስጻቸው አልተመለከትንም፡፡ ይህም የተራበ ሰው በጎዳናው ያገኘው እሸት ቢኖር ከዚያ ቀጥፎ ከረሐቡ እንዲታገስለት ማድርግ የተፈቀደ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ‹‹ወደ ባልንጀራህ ወይን ቦታ በገባህ ጊዜ እስክትጠግብ ድረስ ከወይኑ ብላ ወደ ዕቃህ ግን ከእርሱ ምንም አታግባ። ወደ ባልንጀራህ እርሻ በገባህ ጊዜ እሸቱን በእጅህ ቀጥፈህ ብላ ወዳልታጨደው ወደ ባልንጀራህ እህል ግን ማጭድ አታግባ።›› ዘዳግ 2324-25፡፡  በባለቤቱ ፈቃድ ተካፍለን ወስደን እንደሆነ ይህ ሌብነት አይባልም፡፡  የተወሰደበት ሰው ሳያውቅ - ይሁዳ ደቀ መዛሙርቱ ሳያውቁ ለራሱ እንደወሰደው ወይም ቤቶችን ሰብረው በመግባት ሌቦች እንደሚያደርጉት ያለ ድርጊት ሌብነት ይባላል፡፡ ‹‹ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው።›› ዮሐ 126 ‹‹ሌቦችም ቆፍረው በሚሠርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፡፡›› ማቴ 619፡፡

Monday, December 3, 2012

‹‹አታመንዝር። ›› ዘጸ 20፡14፡፡


አሠርቱ ትእዛዛት - ስድስተኛው ትእዛዝ


1. ከአንድ በላይ ማግባት
 በሐዲስ ኪዳን የተፈቀደው ሕግ አንዲት ሚስት በአንድ ባል፣ አንድ ባልም በአንዲት ሚስት ጸንተው መኖራቸው ነው፡፡ ‹‹ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት።›› ቀዳ ቆሮ 7፡2፡፡
2. ከጋብቻ/ትዳር ውጪ ፈቃደ ሥጋን መፈጸም
 በጋብቻ/በትዳር አጋር ውጪ ፈቃደ ሥጋን - ግኑኝነትን መፈጸም ዝሙት ነው፡፡

3. የቅርብ ዘመድ ማግባት

 ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ከቅርብ ዘመድ ጋር የሚፈጸም ጋብቻ ዝሙት ነው፡፡ ‹‹ዮሐንስ ሄሮድስን። የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና።›› ማር 6፡18፣ ‹‹ከእናንተም ማንም ሰው ኃፍረተ ሥጋውን ይገልጥ ዘንድ ወደ ዘመዱ ሁሉ አይቅረብ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።›› ዘሌዋ 18፡6፡፡ እንዳሉ፡፡ ይህ ዝምድናም መንፈሳዊ ዝምድናን (የክርስትና አባት/እናት ዝምድናን ይጨምራል፡፡)

4. በዝሙት የተፈታውን ወይም የተፈታችውን ማግባት

 በሞት ተለይቶ/ተለይታ ካልሆነ በዝሙት የተፈታውን/ችውን ማግባት ዝሙት ነው፡፡ ‹‹እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ ሁሉ ያመነዝራል፥ የተፈታችውንም የሚያገባ ያመነዝራል አላቸው።›› ማቴ 19፡9፡፡

5. ምኞት

1. ከሰው ወገን ሌላውን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መፈለግ ዝሙት ነው፡፡ ‹‹ወደ ሴት ያየ የተመኛትም ሁሉ ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ
ጋር አመነዘረ፡፡›› ማቴ 5፡28፡፡
2. እግዚአብሔርን ትቶ ሌሎች አማልክትንም ማምለክ የቀናችውንም ሃይማኖት መተው ማመንዘር ነው፡፡ ‹‹ሌሎች አማልክትን
ተከትለው አመነዘሩ ሰገዱላቸውም…›› መሳ 2፡17 እንደተባለ፡፡
 ማመንዘር ከበድ ያለ ኃጢአት ነው፡፡ ‹‹ከዝሙት ሽሹ፤ ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጪ ነው፡፡ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል፡፡›› ቀዳ ቆሮ 6፡18፡፡ እንደተባለ ዝሙት ነፍስንም ሆነ ሥጋን ስለሚያረክስ ነው፡፡ ቀዳ ቆሮ 6፡15-20፣ ዘፍጥ 6፣ ዘፍጥ 19፣ …፡፡ ወደ ክርስትና የተመለሱ አሕዛብ የተሠራላቸው ሕግም ከዝሙትና ከጣዖት አምልኮት እንዲርቁ የሚያሳስብ ነበር፡፡ የሐዋ 15፡19-20፡፡ ስለዚህ ለዝሙት ከሚያነሳሱ ምክንያቶች ሁሉ በመራቅ በጾምና በጸሎት በመወሰን ንስሐ እየገቡ ቅዱስ ቁርባን መቀበል በጽድቅ ታንጸን እንድንኖር ይጠብቀናልና በተጠቀሱት መንፈሳዊ መንገዶች ተወስነን እንድንኖር እግዚአብሔር ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

ምንጭ:
-www.zeorthodox.org/ በቀሲስ ሶሎሞን ሙሉጌታ
-ሕግጋተ እግዚአብሔር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 3ኛ
/ ትርጉም ቀሲስ እሸቱ ታደሰ/ ማኅበረ ቅዱሳን 1995 ዓ.ም