Monday, July 30, 2012

ትዝ ይለኛል



ትዝታ በየሁሉም ሰው ልብና ሕሊና ውስጥ በአጭሩም በረዥሙም በቀጭኑም በወፍራሙም ብቻ በየትኛውም ሁናቴ ቦታ የለውም ማለት አይቻልም፡፡ ትዝታን በዘፈን፣ትዝታን በግጥም፣ትዝታን በንግግር እንዲሁም ትዝታን በማብሰልሰል ማስታወስ የሕይወታችን መቆዘምያ መንገዶች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ትዝታዎቻቸውን ሲያወጉ መስማት በራሱ አንዳች ደስታን ይፈጥራል፡፡ በተለይም ዕድሜ ጠገብ የሆኑ አረጋውያን፡፡ በእውነት የተደረጉ ሳይሆኑ በተለያዩ የተረት መጻሕፍት እንደምናነበው ዓይነት ይሆኑብናል፡፡ ግን እውነቶች ናቸው የተኖሩ፡፡ ለምሳሌ “በ25ሳንቲም ክተፎ በላን” ፣ ”በ15 ሳንቲም በአውቶቡስ ደርሶ መልስ እንጓዝ ነበር፡፡ አንድ ጉዞ ብቻ የሚጓዝ ሰው በቀሪው ማስቲካና ከረሜላ  መለወጥ ይችል ነበር” ፣ “1ኪሎ ጤፍ በ20 ሳንቲም ገዝተናል” እነዚህ እውነታዎች ነገር ግን ትዝታዎች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሃገራችን የተኖሩ ያልተረሱ ትዝታዎች፡፡ እኔ “ምን ትዝታ አልኝ?” ብዬ ራሴን ብጠይቅ ምንም፡፡ ምክንያቱም አኗኗሬ በጥንቃቄና በፍርሃት በሚኖርበት ጊዜ በመሆኑ፡፡ እድለቢስ ነኝ ልበል?
የሆኖ ሆኖ ዛሬ ለመጻፍ የተነሳሁት በ facebook ገጼ ላይ በተደጋጋሚ ጓደኞቼ post እያደረጉልኝ የተመለከትኩት ፎቶ ግራፍ ነው፡፡ ይህ ፎቶ ግራፍ የሰው ወይም የእንስሳ አልያም የሌላ ሥነ ፍጥረት እነዳይመስላችሁ የደብተር እንጂ፡፡ ደብተሩ ላይ ሁለት ወንድና ሴት ተማሪዎች ቦርሳ አንግተው ከኋላቸው የት/ቤት መለያ የሆነው ሰንደቅ ዓላማ እና የመማርያ ክፍሎች ይታዩበታል፡፡ ታድያ ሁሉም ጓደኞቼ post ሲያደርጉልኝ ተመሳሳይ ጽሑፍ አለው፡፡ ከራስጌው ወይም ከግርጌው “በዚህ ደብተር ተምረው ያውቃሉ?” ይላል፡፡ ነገር ግን እስካሁን like’ን ከመጫን በቀር ምንም ምን ሃሳብ አልሰጠሁበትም፡፡ ለምን? እንጃ ብቻ፡፡ ቁንጥር ብትሆንም ትዝታ አለችኝ፡፡ ከደብተሩ በስተጀርባ፡፡

“ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ” ይላሉና አበውና እመው ደብተር ከማያዜ በፊት ቀዳሚውን ላስቀድም፡፡ ትዝታ አይደል የምነግራችሁ? ያለፋችሁበት አብራችሁኝ እለፉ፡፡ ያለላፋችሁበት ደግሞ እንደነበር አስታውሱ፡፡
ቅድመ ታሪክ
 ፊደል
ተወልጄ ላቅመ ቄስ ት/ቤት እስክደርስ ድረስ ያደኩት ልዩ ስሙ ኳስ ሜዳ ወይም በቀድሞው አጠራር ከፍተኛ 7 ቀበሌ 28 ውስጥ ነው፡፡ መቼም ላቅመ ቄስ ት/ቤት ለምን እንዳልኳችሁ መተንተን አያሻኝም፡፡ ምክንያቱ ይገባችኋላ፡፡ ለአጸደ ሕፃናት ወይም ለመዋለ ሕፃናት ብል ትስቁብኛላችሁ እንጂ በጄ አትሉኝማ፡፡ ይሄ የሚታሰበው ለዲታዎችና ለዲታ ልጆች ብቻ ስለነበር፡፡
ወደቀደመው ነገር ልመልሳችሁ፡፡ እንግዲህ ለአቅመ ቄስ ት/ቤት እንደደረስኩ ደብተር ሳይሆን የተገዛልኝ የፊደል ገበታ ነው፡፡ በካርቶን ላይ የተለጠፈች ፊደል፡፡ ከራስጌዋ “ያልተማረ ይማር!” ይላል፣በግራ ጎኗ በኩል ቁልቁል “መሃይምነት የጨለማ ጉዞ ነው!” የሚሉ መፈክር መሰል ነገር ግን ቁም ነገራቸው ያየለ ዓረፍተ ነገሮች ተጽፈውባቸዋል፡፡ ያነበብኳቸው ግን ከአራተኛው ፊደል ቅያሪ በኋላ ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል ከፊደሉ ጋር የተሰጠኝ እርሳስ ወይም እስክሪብቶ አልነበረም ሴት አያቴ ጠርታኝ “ልጄ ተማሪ ቤት ሲኬድ ፊደሉ ብቻ ሳይሆን መቁጠሪያም ያስፈልገዋል እነሆ” ብላ ሰጠችኝ፡፡ ምን? አትሉኝም በስንት ብር እንደተገዛ ከማላውቀው የእንጀራ መሶብ ላይ ስንደዶ መዛ፡፡ በቃ የኔ እስክሪብቶዬና እርሳሴ ስንደዶ ነበር፡፡ ፊደል ቆጥሬ እስከምጨርስ፡፡ ትዝ ይለኛል አስተማሪያችን በጣም ኃይለኛ ነበሩ፡፡ አሁን ይለፉ በሕይወት ይኑሩ አላውቅም፡፡ ት/ቤቱ እንደሌለ ግን ሰምቻለህ፡፡ ወሬ፡፡ እሳቸው ዘንድ ያልተማረ ማንም የለም፡፡ እኔ ልመዘገብ በሄድኩ ጊዜ እንኳ ዶክተር እከሌ/እከሊት፣መምህር/ት እከሌ፣ነርስ… ወዘተርፈ እሳቸው ጋር ከፊደል እስከ ዳዊት ደግመዋል፣ተምረዋል ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ማነቃቅያ ነገር ነበር መሰለኝ፡፡ ማናቸው እሳቸው አትሉኝም ታድያ “ስቡዬ”፡፡ “የኔታ” ሲባሉ ሰምቼ በጭራሽ አላውቅም፡፡ ኃይለኛ ናቸው ብያችሁ አልነበር፡፡ ስቡዬ ቁጭ ነው የሚሉት፡፡ ቁጭ ብቻም አይሉም በተቀመጡበት እንቅልፍ ይወስዳቸውማል፡፡ ቁጭ ባሉበት ይወዛወዛሉ፡፡ ከእጃቸው ላይ የነጭ ባህር ዛፍ ልምጭ አይታጣም፡፡ ከቀራንዮ አካባቢ ነበርና የሚመጡት፡፡ መኪና የላቸውም አህያ ግን ነበራቸው፡፡ አህያው ወንድ ይሁን ሴት ትሁን ትዝታዬ ውስጥ የለም፡፡ ልምጩ መጀመሪያው አህያቸውን መንጃ ነው ፍፃሜው የተማሪዎቻቸው ጀርባ፡፡ ቀድሞ የገባ ነባር ተማሪ ወይም ካሉት ተማሪዎች መካከል ከፍ ያለ ነው ብለው ያሰቡትን አለቃም ፊደል አስቆጣረም አድርገው ይሾሙታል፡፡ ይኽ ሹመት ሳይደርሰኝ ት/ቤቱን መልቀቄ ትዝ ይለኛል፡፡  
እናላችሁ “ሀ ሁ ሂ …..ሆ” እያለ አስቆጣሪው ሲያስቆጥረን አልፎ አልፎ ድምፃችን ከፍ ይልና ጋሼን እንቀሰቅሳቸዋለን፡፡ በዛች ቅፅበት ዓይኑን ከፊደል ገበታው ላይ አንስቶ ወደሌላ አቅጣጫ ሲመለከት ያዩትን ተማሪ አባቴ ይሙት ምን አይነት ጭካኔ ነው በዛ በነገርኳችሁ ልምጭ የዕለቱን ጸሎት ያስጀምሩበታል፡፡ ከዛ በኋላ ቀጭን ትዕዛዝ ያዙና ይወጣሉ፡፡ ተከትሎም ጥንድ ጥንድ ሆነን ጣቶቻችንን አቆራኝተን ስንደዷችንን ጨብጠን ፊደላችንን እንቆጥራለን፡፡ እሳቸው ምሳ ሰዓት ሲደርስ ወደቤት ለማለት በአህያቸው አተላ ጭነው ይመለሳሉ፡፡ እኛም እንለቀቃለን፡፡ ከሰዓት በኋላ ለመመለስ ምጥ ነው፡፡ ለምን ቢሉ የከሰዓቱ ቅጣት በሳማ ነውና፡፡ ጀርባችን ውስጥ ሳማውን ከተው ያሹናል፡፡ ጨካኝ ናቸው አይደል? ቢሆኑም ቅሉ ባለውለታዬ ናቸው፡፡ ፊደል አሳውቀውኛል አቡጊዳ አስነብበውኛል ደግሞም መልዕክተ ዮሐንስን በሚገባ አስደግመውኛል፡፡ አመሰግናለሁ ጋሼ፡፡
ከሳቸው ጋር ወጥቼ ሌሎች ቄስ ት/ቤቶችም ተምሬአለሁ፡፡ ከሁሉም ትዝ የሚለኝ አዲሱ ሚካኤል መዳረሻ የነበረው ቄስ ት/ቤት ነው፡፡ ከትምህርቱ ይልቅ ሽታው ትዝ ይለኛል፡፡ የምን ሽታ ነበር? ትዝ አለኝ የ”ብቅል”፡፡ ለመቀመጫነት የሚያገለግሉን ከስራችን ለተነጠፈው ብቅል ማብቀያነት የሚያገለግል ላስቲክ መደገፊያነት የተደረደሩ ድንጋዮች ነበሩ፡፡ እንደ ስቡዬ ድንጋዮቹ ላይ ጣውላ የለም ድንጋዮች ብቻ፡፡ ውይ ሲያም አሁን መሰለኝ፡፡
ትዝ ይለኛል ወደ ቄስ ት/ቤት ስሄድ እንደአሁኖቹ ዕድለኛ ልጆች ቦርሳ፣ተደራራቢ ምሳ ዕቃ፣ ውሃ/ለስላሳ/ የምይዝበት ኮዳ አልነበረኝም፡፡ ይልቁንስ ዕድለኛ የሆንኩ እነደሆነ በተለይም ዓመት በዓል ሰሞን ከሆነ የዱቤ ዱቄት ላስቲክ ጫፍና ጫፉ በሚስማር ተበስቶ በቃጫ ይታሰርና በጀርባዬ እንዳዝለው ይደረጋል፡፡ እድል ፊቷን ያዞረችብኝ እንደሁ ካኪ ኪስ ወረቀት ተፈልጐ ፊደሌን በሱ እጠቀልላት ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል ውሃ ለመያዝ ተገኘ ከተባለ የሽሮፕ ብልቃጥ ነው፡፡ ውሃ ተሞልቶ ይሰጠኛል፡፡ ልብ በሉ ውሃ ብቻ፡፡ እኔ ግን አንድ እሴት እጨምርበታለሁ፡፡ የተሰጣ የሽሮ ክክ ሰርቄ ብልቃጤ ውስጥ እጨምርበታለሁ፡፡ ከዛም ቄስ ት/ቤት ውስጥ እርሱም የሌላቸውን ተማሪዎች እንቁልልጭ እያልኩ እውል ነበር፡፡ አይ ጊዜ ትዝታው፡፡
ትዝ ይለኛል ፊደል ስንቆጥር ተቃቅፈን ስንወዛወዝ፡፡ ደስታው ምን ያህል እንደሆነ ያለፋችሁበት አብራችሁኝ እለፉ፡፡ ያለላፋችሁበት ደግሞ እንደነበር አስታውሱ፡፡ ይህ መተቃቀፍ ታድያ እርስ በርስ ለነበረን መከባበርና መፈቃቀር ከፍተኛ ድርሻ ነበረው፡፡ ስቡዬን የሚያወዛውዛቸው ግን እንቅልፍ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ስንታሽ የምንውልበት መቀመጫችን አካባቢ ያለው የሱሪያችን …አያይ ወዲህ ነው የቁምጣችን /ባለማንገቻው ነው/ ክፍል በወንበራችን ጣውላ ተበልቶ መሃሉ ሲተርፍ በሁለቱ ክፍል ያለው ቦታ እንደ መስኮት ወከክ ብሎ ይከፈታል፡፡ ይሁን እነጂ አይታወቀንም፡፡ መቼ ነው የሚታወቀን አንዳንድ ክፉዎች ልጆች ከኋላ ኋላችን እየተከተሉ “ባለ መነጽር…ባለመነጽር…” በዜማ ሲሉን እናስታውሰውና አንዳችን የአንዳችንን ስንምለከት አፈር እንጂ የሰው ገላ አይምስልም ነበር፡፡ ቁምጣችን በመቀደዱ ምክንያት የሚገዛልን ሰው የለም፡፡ አሮጌ ጨርቅ ተፈልጎ መጣፊያ ይጣፍበታል እንጂ፡፡ አዲስ ቁምጣ ቢያምረንም ከእንቁጣጣሽ ወዲህ ማን ይገዛልናል? ማንም፡፡
ደብተሩ
ትዝ ይለኛል ደብተር የያዝኩት ከኳስ ሜዳ ለቅቄ ወደ ሳሪስ ከተዛወርኩ በኋላ ነው፡፡ እናቴ በማኀበር ታቅፋ ወደሠራችው የቁጠባ ቤት፡፡ መንግስቱ ኃ/ማርያምን ሁሌም ስታመሰግነው እሰማታላሁ፡፡ የራሷ የሆነ ቤት ስለሰጣት ይሆናል፡፡ ሰፈሩ ሳሪስ ዲሱ ሰፈር ይባላል፡፡ መንደሩ ገና አዲስ ስለነበረ ምንም ት/ቤት አልነበረበትም፡፡ በዙሪያው ግን በርካታ የሕዝብም የመንግስትም ት/ቤቶች ሞልተዋል፡፡ ተመስገን ነው፡፡ 1ኛ ክፍል ገብቼ ደብተር ሊገዛልኝ ነው፡፡ በቃ ከቄስ ት/ቤት ወደ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪነት ልዛወር ነው፡፡ አቤት ደስታ አቤት ሐሴት፡፡ የምምዘገብበት ት/ቤት ተመረጠልኝ፡፡ፍሬሕይወት ቁጥር 2 1ኛ ደረጃ የሕዝብ ት/ቤት፡፡ ተመዘገብኩ መመዝገብ ብቻውን ግን በቂ አልነበረም ፈተና መፈተን ግድ ይላል፡፡ ትዝ ይለኛል ፈተናዎቹ ሙሉ ስም መጻፍና በቀኝ እጅ በኣናት ላይ አሳልፎ ግራ ጆሮን መንካት ነበሩ፡፡ ሁለቱንም አለፍኩ በቃ አሁን ደብተር ሊገዛልኝ ነው፡፡ ምስጋና ለስቡዬ ይሁን፡፡ ጆሮ መንካቱን ግን ለምን አላስተማኝም?
ሆኖም ደብተር መግዛት እንዲህ በዋዛ የሚገኝ አልሆነም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ደብተር ለመግዛት የቀበሌ ነዋሪነት መታወቂያና የህብረት ሱቅ ራሽን ካርድ ሊኖር ግድ ይላል፡፡ ያም ኖሮ ወረፋው በወራት አይደርስም፡፡ የምነግራችሁ ትዝታ እኮ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ ደብተር የመያዝ ህልሜ እዚህ ላይ አበቃ፡፡ ወረፋው ተይዟል ግን ለ2ኛ ክፍል ይደርስልኝ ካለሆነ በቀር ላሁኑ ሊያልፈኝ ነው፡፡ ይለፈኛ፡፡
ጉጉቴ ውሃ በላው ደብተር የለኝም፡፡ ባዶ እጄን ክፍል ስገባ አስተማሪዎቼ በየተራ “ማሪቱ” በምትስኝ ጎማ የወጥር እያስያዙ መቀመጫዬን ይልጡት ያዙ፡፡ ዘጠኝ ናቸው፡፡ ቄስ ት/ቤት ውስጥ የጣውላ ወንበር ይቀደው የነበረውን አሁን በተራው የሞተር መዘወርያ ችንጋ ይቀደው ዘንድ ተተካ፡፡ ትዝ ይለኛል የእጅ ሥራና ስዕል አስተማሪዎቼም የድርሻቸውን ይናጠቁኝ ነበር፡፡ የነሱ ግን ይለያል፡፡ በማስመሪያ በአይበሉባዬ በኩል  ገልብጠው ይቀለጥሙኛል፡፡ ይህ ሁሉ ታድያ የሚሆነው ደብተር ስለሌለኝ ነበር፡፡ ለምን እንደሌለኝ አንዳቸውም ጠይቀውኝ አያውቁም፡፡ የነርሱ ድርሻ እየተፈራረቁ እንደማርያም ጠላት እኔን መውገር እንጂ፡፡ ከዛ በኋላ ለረዥም ዓመታት አይናፋርነት ተጠናውቶኝ ቆይቻለሁ፡፡ ድሃ ባልሆን ኖሮ እኮ ቀበሌ ወረፋ ሳይጠበቅ ከማከፋፈያ ይገዛልኝ ነበር፡፡ በቃ አልናገር አልጋገር ሰው ቀና ብሎ ማየት ሞት ይመስለኝ ነበር፡፡ ዓይናፋሩ ልጅ እየተባልኩ አደኩ፡፡ ይሄ ሁሉ ታድያ በደብተሩ ምክንያት ነው፡፡
ትዝ ይለኛል ደብተር የመገኘቱ ነገር በመሟጠጡ ታላላቅ ወንድሞቼ የተማሩባቸው ደብሮች ከያሉበት ተበርብረው ወጥተው ያልተጻፈባቸው ባዶ ወረቀቶች ከመሃል እየተገነጠሉ መጠናቸው ቢለያይም በክር እየተሰፉ ደብተሮች ሆኑልኝ፡፡ ይሄን ያላሳጣኝ አማላኬን አመሰግነዋለሁ፡፡ ሆኖም በነዚህ የተሰፉ ደብተሮች የደብተር ማርክ ማግኘት ዘበት ነበር፡፡ እንኳን ለማርክ ላመጻፍ እንኳ ከቦርሳዬ ሳወጣቸው ድንቄም ቦርሳ …እየተሸማቀኩ ነበር፡፡ ለምን ብትሉ ቦርሳዬ ከሸራና ላስቲክ ተረፈ ምርት የሚሰራ ቦርሳ ስለነበረ ደብተር ለማውጣት በከፈትኩት ቁጥር ሽታው አስቀያሚ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ገበሩ እንደማስቲካ ያለ ተሳቢ ነገር ስለሆነ አንዳንዶች ሰርቀውኝ አንዳነዶችም አስፈቅደውኝ እየላጡ ያኝኩት ነበር፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች ጓደኞቼ የሾፌር ልጆች/የኤርትራ ክፍል ሃገር/ ተወላጆች በመሆናቸው ከኣሰብ ወይም ከሌላ ቦታ የሚመጣላቸው ቦርሳ ዲኖ/DINO/ ይሰኝ ነበር፡፡ የወቅቱ ምርጥ ቦርሳ ነው፡፡ እኔ ግን ደብተር የለኝም አላልኳችሁም፡፡
ትዝ ይለኛል በስንት አማላጅና ሰው በሰው ትውውቅ ለ2ኛ ክፍል ደብተሩ ደረሰልኝ፡፡እንኳን ደስ አለህ አትሉኝም፡፡ ያ ደብተር ታድያ ከላይ የምታዩት አይነቱ ሳይሆን “መሬት ላራሹ” የሚል ጽሑፍ ያለበት የጥቁር ጤፍ ቂጣ የመሰለ መልከመልካም ሽፋን የነበረው ነበር፡፡ እዚህ ላይ የምታዩትን ደብተር ለመያዝ የታደልኩት ከ2ኛ ክፍል ስሻገር ነው፡፡ ደብተሩ ታድያ አልፎ አልፎ ባለ ሁለት ኮት ይገኝበታል፡፡ የተደረበውን ኮት ስገነጥለው ኤርትራም ሃገር ሆነች፡፡ ሌሎች ትዝታዎች ካሉኝ በሌላ ቀጠሮ አስተዝታችኋለሁ፡፡ አበቃሁ፡፡ እናንተስ?
ሐምሌ 23 ቀን 2004 ዓ.ም

8 comments:

  1. "ጉጉቴ ውሃ በላው ደብተር የለኝም፡፡ ባዶ እጄን ክፍል ስገባ አስተማሪዎቼ በየተራ “ማሪቱ” በምትስኝ ጎማ የወጥር እያስያዙ መቀመጫዬን ይልጡት ያዙ፡፡ ዘጠኝ ናቸው፡፡ ቄስ ት/ቤት ውስጥ የጣውላ ወንበር ይቀደው የነበረውን አሁን በተራው የሞተር መዘወርያ ችንጋ ይቀደው ዘንድ ተተካ፡:" betam arif tizita new enen ayehubet

    ReplyDelete
  2. ejig betam betam konjo yehone akerareb new wedijewalehu

    ReplyDelete
  3. "ስቡዬ ቁጭ ነው የሚሉት፡፡ ቁጭ ብቻም አይሉም በተቀመጡበት እንቅልፍ ይወስዳቸውማል፡፡ ቁጭ ባሉበት ይወዛወዛሉ፡፡ ከእጃቸው ላይ የነጭ ባህር ዛፍ ልምጭ አይታጣም፡፡ ከቀራንዮ አካባቢ ነበርና የሚመጡት፡፡ መኪና የላቸውም አህያ ግን ነበራቸው፡፡ አህያው ወንድ ይሁን ሴት ትሁን ትዝታዬ ውስጥ የለም፡፡" yeneta tiz alugn bernabas ameseginalehu

    ReplyDelete
  4. እጅግ በጣም ደስ የሚል ጽሁፍ ነው እኔም ወደ ኋላ የኔታን አስታወስኳቸው ……. “እናላችሁ “ሀ ሁ ሂ …..ሆ” እያለ አስቆጣሪው ሲያስቆጥረን አልፎ አልፎ ድምፃችን ከፍ ይልና ጋሼን እንቀሰቅሳቸዋለን፡፡ በዛች ቅፅበት ዓይኑን ከፊደል ገበታው ላይ አንስቶ ወደሌላ አቅጣጫ ሲመለከት ያዩትን ተማሪ አባቴ ይሙት ምን አይነት ጭካኔ ነው በዛ በነገርኳችሁ ልምጭ የዕለቱን ጸሎት ያስጀምሩበታል፡፡”…..ወይ የቄስ ቤት ትዝታ…. እናመሰግናለን ልጂ በርናባስ

    ReplyDelete
  5. yemigerim new enem yesibuye temari neberku minalbatim kante bebizu kedime bezih huneta yitawesalu biye gin altebekum ....betam des bilognal ye kuas meda lij berta

    ReplyDelete
  6. "ደብተሩ ታድያ አልፎ አልፎ ባለ ሁለት ኮት ይገኝበታል፡፡ የተደረበውን ኮት ስገነጥለው ኤርትራም ሃገር ሆነች፡፡" asgerami kine new lelam entebikalen wendim Bernabas

    ReplyDelete
  7. Bernabas lewedefitu tiru tsehafi endemiwetah megemet yichalal berta bezih atakum lelechinim negeroch eyetemeleketk asnbiben...(Bernabas min malet new)

    ReplyDelete