Wednesday, October 10, 2012

አምስተኛ ትእዛዝ


ክፍል

 ‹‹አትግደል።›› ዘጸ 2013፡፡
አባትና እናትን አለማክበር፣ ሰንበትን አለማክበር፣ ጥንቆላበሞት ያስቀጡ ነበር፡፡ ዘሌዋ 2010-16 ዘሌዋ 2114-29 ዘጸ  3114 ዘጸ 2220 ዘሌዋ 2416 ቀዳ ነገ 1840 ዘሌዋ 2027 ዘጸ 2116፡፡ በብሉይ የገደለ እንዲገደል ታዞ ነበር፡፡ ዘፍጥ 96 ሮሜ 1314፡፡ በሐዲስ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ማቴ 2652፡፡  ለእንስሳትና ለሌሎች ፍጥረታትም የሚጎዱን እስካልሆኑ ድረስ እንራራላቸው ዘንድ ይገባናል፡፡ ማቴ 1029፡፡ በምንሠራው በእያንዳንዱ ኃጢአት ሰውን ቅር የምናሰኝ ብንሆንም መግደል ግን ሰውን በዚህ ዓለም የተሰጠውን የመኖር ዕድል እንዳይጠቀምበት የምናደርግበት ኃጢአት ነው፡፡ ይልቁኑ ንስሐ ያልገባን ሰው መግደል እጅግ የሚበዛ በደል ነው  መልካምነት የበዛላቸውን ሰዎች መግደል ኅብረተሰቡን መግደል ነው፡፡ እንዲህ ባለ መንገድ የሚበድሉትንም እግዚአብሔር ይበቀላል፡፡ ራእ 610፡፡  አትግደል የሚለው ሕግ ራስህንም ሆነ ሌላውን አትግደል ማለት ሲሆን አውዳሚ መሳሪያዎችን መጠቀምም በዚህ ሕግ የተከለከለ ነው፡፡ ችሎታችንን፣ እውቀታችንን፣ ብቃታችንን ሁሉ ሰውን ለሚያጠፋ ምክንያት መጠቀም በዚህ ሕግ የተከለከለ ነው፡፡ ከፍ ባለ አደጋ ጊዜ ግን ራስን መከላከል አልተከለከለም፡፡ በዓለማችንም ሕግ በጦርነት ጊዜ ሕጻናት፣ ሴቶችን፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ ካህናትን፣ መነኮሳትን፣ ሕሙማንን መጉዳትም አልተፈቀደም፡፡ ይህም ዓለማችንን ከጭካኔ ድርጊት ለመታደግ የተደረገ ነው፡፡ በርግጥ ገዳዮች የሚደነቁበት የሚፈሩበት አጋጣሚ ቢኖርም የወንድሞቻቸው ገዳዮች ናቸው፡፡

በመስለብ  መግደል
የወንዱን አባለ ዘር በማጉደል ዘር እንዳይተካ በቁሙም ሙት እንዲሆን ማድረግ በጭካኔ ከመግደል ይቆጠራል፡፡ ይህም የጭካኔ ድርጊት በጥቁሮች ሕዞቦች ላይ ተፈጽሟል፡፡ በአውስትራሊያ በሚገኙ አቦርጅናሊስቶች የተፈጸመውም ይኸው ነው፡፡
ጽንስ  በማስወረድ መግደል
ጽንስ ሕይወት ያለበት ሰው ነው፡፡ ማስወረድም ሆን ተብሎም ሆነ ለዚህ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ሊፈጸም ይችላል፡፡  አንዳንድ ጊዜ እናቲቱን ለማዳን ሲባል ጽንሱን የመግደል ድርጊት ይፈጸማል፤ ይህም ለጉዳቱ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉትን ከአቅም በላይ ሥራ የሚያሠሩ አሠሪዎችን ወይም ለነፍሰ ጡር ሚስቶቻቸው ተገቢውን እንክብካቤ ያጎደሉትን ባሎች ግን ከተጠያቂነት ነጻ አያወጣም፡፡ በአጠቃላይ ግን ጽንስን ማስወረድ መግደል ነው፡፡
በሐሳብ መግደል
በተግባር የመግደልን ድርጊት ባንፈጽመውም እኛ ወይም ሌሎች እንዴት እንደሚገድሉልን ማሰብ፣ በፊታችን ቢሞትም ደስታ የሚሰማን ሆኖ በሐሳብ መመላለስም ከመግደል የሚቆጠር መንፈሳዊ ኃላፊነትን የሚያስከትል ነው፡፡ ይህም ወደሴት አይቶ እንደመመኘት ነው፡፡  ለመግደል ማሰብ ከፍቅር፣ ከመቻቻል፣ በጎ ነገርንም ከማሰብ ጋር አብሮ አይሄድም፡፡  ለመግደል ባይቻለንም የሰውን ሞቱን የምንመኝ፣ ቢሞትልን ወይም እግዚአብሔር ሕይወቱን ቢወስዳት የምንደሰት መሆን መግደል ነው፡፡ ‹‹ወንድሙን የሚጠላ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው›› እንደተባለ ጥላቻ ቀዳ ዮሐ 315 ያላግባብ መቆጣትም መግደል ናቸው፡፡ ማቴ 521-22፡፡
ሞራልን መግደል
 የሰውን ሞራል የሚጎዳ የመግደል ዓይነትም ስላለ መግደል አካላዊ ብቻ አይደለም፡፡  አንድ ሰው የሰውን ክብር/ስም/መልካም ምግባር የሚያጎድፍ ንግግር መናገር ስምን ማጥፋት በሰዎችም ዘንድ ክብርን መንካት የሞራል ግድያ ይባላል፡፡  ሰውን ሆን ብሎ በሰው ፊት ይናቅ ዘንድ ዋጋ የሚያሳጣውን ነገር ማድረግ ያን ሰው እንደመግደል ይቆጠራል፣ ብዙ ጊዜ ሰዎች ይህን የሚያደርጉትም በምናደርገው ያበቃለታል ይጠፋል ብለን አስበን ስለሆነ ከመግደል ይቆጠርብናል፡፡ ተገቢ ያልሆነ ትችትም ሌላው መግደል ነው፡፡  ሚስቶቻቸውን የሚጎዱ ባሎች፣ ሠራተኞቻቸውን የሚያስመርሩ አሠሪዎች፣  ልጆቻቸውን ሞራል የሚጎዱ ወላጆች እንደ ገዳይ ይቆጠራሉ፡፡
መጠነኛ ግድያ
መደብደብ፣ ማቁሰል፣ ዓይንን እግርን ወይም ፊትን መጉዳት ማጉደል እንደመግደል ይቆጠራሉ፡፡ ‹‹እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል፤ ወንድሙንም ጨርቃም የሚለው ሁሉ የሸንጎ ፍርድ ይገባዋል፤ ደንቆሮ የሚለውም ሁሉ የገሃነመ እሳት ፍርድ ይገባዋል።›› ማቴ 522፡፡
ቀጥተኛ ያልሆነ ግድያ
 ሰው ነርቩ እስኪጎዳ፣ ራሱን መቆጣጠር እስኪሳነው እንዲናደድና እንዲሞት ምክንያት ሆነን በሞቱ ጊዜ በለቅሶው ቤት ተገኝተን ማስተዛዘን እንደ ገዳይ ከመቆጠር ነጻ አያደርግም፡፡ ‹‹ምላሳቸው የተሳለ ፍላጻ ነው ሽንገላን ይናገራሉ ሰው ከባልንጀራው ጋር በሰላም ይናገራል፥ በልቡ ግን ያደባበታል።›› ኤር 98 ‹‹አፉ ከቅቤ ይልቅ ለዘበ፥ በልቡ ግን ሰልፍ ነበረ ቃሎቹም ከዘይት ይልቅ ለሰለሱ፥ እነርሱ ግን እንደ ተመዘዘ ሰይፍ ናቸው።›› መዝ 5421፡፡
ሠራተኞችን ያላግባብም መበደል መግደል ነው፡፡
 ጥቂት ደመወዝና ምግብ እየሰጡ የሚያሠሩ ባለጠጎች ነፍሰ ገዳይ ናቸው፡፡ ደመወዛቸው ሊሻሻል ሲገባው ቸል የሚሉ የሚነፍጉም እንዲሁ ይቆጠራሉ፡፡ ‹‹እነሆ፥ እርሻችሁን ያጨዱት የሠራተኞች ደመወዝ በእናንተ ተቀምቶ ይጮኻል፥ የአጫጆችም ድምፅ ወደ ጌታ ፀባዖት ጆሮ ገብቶአል።›› ያዕ 54 ዘሌ 1913 ዘዳግ 2414-15፡፡ አበድሮ ማስጨነቅም በዚህም የተነሳ ለሞት ማብቃት ከደጋይነት ያስቆጥራል፡፡ ዘጸ 2225 ዘዳግ 2417፡፡
መርዳት ስንችል አለመርዳትም እንደ መግደል ነው፡፡
አንድ ሰው በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ ባንረዳው እንደ መግደል ይቆጠራል፡፡ ‹‹የድሀውን ጩኸት እንዳይሰማ ጆሮውን የሚደፍን ሰው፥ እርሱ ራሱ ይጮኻል አይሰማለትምም።›› ምሳ 2113፡፡  ለተራቡት በቂ ምግብ እያለን አለመርዳት እንደ መግደል ይቆጠራል፡፡ ያዕ 417፡፡ መድኃኒት ማቅረብ ወይም የድሆችን
ጩኸታቸውን መስማት እየቻልን አለመስማት እንደመግደል ይቆጠራል፡፡ ሉቃ 1619-22 ማቴ 913፡፡ ኃላፊነትን ተቀብሎ መግደል  በግድየለሽነት በሠራነው ሕንጻ፣ በምናሽከረክረው መኪናየሰው ሕይወት ላይ በሚደርስ አደጋ ገዳዮች ሆነን እንቆጠራለን፡፡  ልጆችን አላግባብ የሚያሳድግ ወላጅ፣ ሠራተኞቹንም በአግባብ የማያስተዳድር አሠሪ በመጨረሻ በሚደርስ ታላቅ አደጋ የተነሳ እንደ ገዳይ ሊቆጠሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ መድኃኒትን ሳይቀር ከልጆች አርቀን በማስቀመጥ እንጠንቀቅ፡፡
ነፍስን መግደል
 እውነተኛይቱን ሃይማኖት ከማወቅ መከልከል፣ እንግዳ ሃይማኖትንም መፍጠር መግደል ነው፡፡ ‹‹አባቶችህ የሠሩትን የቀድሞውን የድንበር ምልክት አታፍልስ።›› ምሳ 2228 ኤር 616፡፡  ‹‹ወንድሞቼ ሆይ፥ ከእናንተ ብዙዎቹ አስተማሪዎች አይሁኑ፥ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና። ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።›› ያዕ 31-2፡፡
እረኝነትን ጥበቃን ቸል ማለት
ሕዝ 317-19 ‹‹ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ።›› ሆሴ 46፡፡ ቀዳ ሳሙ 229-34፡፡  ነገርን ሳያጣሩ ሳይመረምሩ ሰውንም ወደ ንስሐ ሳያቀርቡ መፍረድ እንደመግደል ይቆጠራል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነትዋ ሰዎችን ማዳን እንጂ መግደል አይደለምና የቤተ ክርስቲያን የሆኑ ሁሉ የራቀውን ለማቅረብ በርትተው በተቻላቸው ሁሉ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ሰው በራሱ ፈቅዶ ወስኖ ካልሆነ ከእኛ ባጎደልነው ወደ ሞት ብንነዳው እንደ ገዳይ መጠየቃችን አይቀርም፡፡ሉቃ 172፡፡
ራስን መግደል
 ሲጋሬ ማጤስ፣ አልኮል መጠጦችን መዘውተር፣ አደንዛዥ እጽ መጠቀምከፍ ሲልም በተለያዩ ነገሮች ተመርሮ እግዚአብሔርን በትዕግሥት ከመጠበቅ ይልቅ ራስን መግደል አልተፈቀደልንም፡፡
ማጠቃለያ
ሰው ራሱ ተጠቦ ራሱን የፈጠረ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ መግደልም ሆነ ማዳን የፈጠረው የእግዚአብሔር ሥልጣን ነው፡፡  ‹‹እግዚአብሔር ይገድላል ያድናልም፡፡›› ቀዳ ሳሙ 26፡፡ የሚለው ኃይለ ቃል መግደልና ማዳን በሚቻለው በእግዚአብሔር ሥልጣን ጽኑ እምነት እንዲኖረን የሚያስገነዝብ ሲሆን በዚህ አሠራር ጣልቃ ገብተን መግደል መልሰን ማዳን የማንችለውን የሰውን ሥጋ ብቻ ሳይሆን ንስሐ ያልገባውን ሰው ነፍስም የመግደል አደጋ ውስጥ ሊከተን እንደሚችል የሚያስታውሰን ነው፡፡ ‹‹ዳሩ ግን የሚፈሩና የማያምኑ የርኵሳንም የነፍሰ ገዳዮችም የሴሰኛዎችም የአስማተኛዎችም ጣዖትንም የሚያመልኩ የሐሰተኛዎችም ሁሉ ዕድላቸው በዲንና በእሳት በሚቃጠል ባሕር ነው፤ ይኸውም ሁለተኛው ሞት ነው።›› ራእ 218፡፡  ቅዱሳን ሰዎች በሞታቸው በእግዚአብሔር ፊት የሚጠቀሙበት የክብር አክሊል የሚቀበሉበት ቢሆኑም በቅድስናቸው የሚጠቀሙባቸውን ምዕመናንን ግን ይጎዳል፡፡
በሥነ ፍጥረት መጀመሪያ ቃየል አቤልን ሲገድለው ‹‹እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፦ ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? እርሱም አለ፦ አላውቅም የወንድሜ ጠባቂው እኔ ነኝን? አለውም፦ ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል። አሁንም የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ።›› ዘፍጥ 29-11፡፡ በማለት እግዚአብሔር ተናግሮአል፡፡  ንስሐ ያልገባ ሰው በደም በተጨማለቀ እጁ መንፈሳዊ ሥራ ለመሥራት ቢነሳ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውም  ልበ አምላክ ዳዊት የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለመሥራት በፈለገ ጊዜ  ከለከለውም በዚሁ የተነሳ ነበር፡፡ ቀዳ ዜና 228፡፡  በግፍ ለተገደሉት ሁሉ የሚበቀልላቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ዘሌዋ 1918 ዘፍጥ 35 ሮሜ 1219፡፡  አንድ ሰው ገደለ የሚባለው በሐሳብ ጸንሶ፣ በንግግር ወልዶ በግብር ሲፈጽመው ነው፡፡ ስለዚህ መግደል እነዚህን ሦስት መልኮች መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ‹‹ወደ ሴት ያየ የተመኛትም ሁሉ በልቡ አመነዘረባት፡፡›› ማቴ 528 ‹‹እኔ እላችኋለሁ ሰዎች ስለሚናገሩት ስለ ከንቱ ነገር ሁሉ በፍርድ ቀን መልስ ይሰጡበታል፤ ከቃልህ የተነሳ ትጸድቃለህና ከቃልህም የተነሳ ትኮነናለህ፡፡›› ማቴ 1236-37 ‹‹ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።›› ቀዳ ቆሮ 618፡፡
1. አካልን መግደል
መግደል አንድን ሰው ለመግደል ማሰብ፣ በሌላ ሰውም እጅ እንዲገደል መመኘት፣ ያላግባብ መቆጣት፣ ጽንስን ማስወረድንም የሚጨምር ነው፡፡ ‹‹ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ።›› ቀዳ ዮሐ 315 ማቴ 521፡፡
 የሚያሳዝን ንግግር መናገር፣ በስድብና ንቀት የሰውን ኅሊና ማቁሰል፣ የሠራተኞችን ደመወዝ መንፈግና በግፍ ጉልበታቸውን መበዝበዝ፣ ፍርድ  ጓደል፣ ያለ በቂ ምክንያት ሠራተኞችን ከሥራ ማባረር፣ በረሐብ ወይም በሌላ ምክንያት ሞት ላጠላበት ሰው በግድ የለሽነት ወይም በጭካኔ የተነሳ ቸል ብሎ ማለፍም መግደል ነው፡፡ ዘሌዋ 193 2414 ያዕ 514 ምሳ 2113፣ ያዕ 417 ሉቃ 1619፡፡ የሚያስረዱንም ሰውን መግደል ተኩሶ፣ ጦር ወርውሮ፣ ዱላ ሰንዝሮ፣ ድንጋይ ወርውሮ መግደል ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡
2. ነፍስን መግደል
 ነፍስ የምትሞተው ከእግዚአብሔር ስትለይ ነው፡፡ በአምልኮተ እግዚአብሔር የሚኖረውን ሰው ወደ አምልኮተ ጣዖት፣በጽድቅ የሚኖረውን ወደ ኃጢአት መግፋት በሃይማኖት የሚኖረውን መደ መናፍቅነት መለወጥ ነፍስን መግደል ነው፡፡  የነፍስ አባቶችም ልጆቻቸውን መክረው አስተምረው መጠበቅን ትተው ለጥፋት አሳልፈው የሚሰጡ ከሆነ ነፍሰ ገዳዮች ናቸው፡፡ ‹‹ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ። የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ ስለዚህ የአፌን ቃል ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። እኔ ኃጢአተኛውን፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቅ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።›› ሕዝ 316-19 ዘዳግ 66-7፡፡
3. ራስን መግደል
 ችግር ሲበዛ መከራም ሲጸና ታግሦ እግዚአብሔርን መጠበቅ እንጂ ራስን መግደል አልተፈቀደም፡፡ ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ መፍትሔ አይገኝበትምና፡፡
 ሃይማኖትን መካድና ኃጢአትንም መሥራት ራስን መግደል ነው፡፡ ሮሜ 87፡፡ እንዲህ የሞተ ሰውም ከጾም፣ ከስግደት፣ ከምጽዋት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከመመልከት፣ ከንስሐ፣ ከሥጋ ወደሙ፣ ከምስጋና፣ ይርቃል፡፡  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።›› ቀዳ ቆሮ 316-17፡፡ እንዳስተማረን ሰውነታችንን በንስሐ መልሰን ማነጽ ያስፈልገናል፡፡
 ‹‹ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፥ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል። እጃችሁ በደም ጣታችሁም በበደል ረክሳለች፥ ከንፈራችሁም ሐሰትን ተናግሮአል፥ ምላሳችሁም ኃጢአትን አሰምቶአል። በጽድቅ የሚጠራ በእውነትም የሚፈርድ የለም በምናምንቴ ነገር ታምነዋል ሐሰትንም ተናግረዋል ጕዳትን ፀንሰዋል በደልንም ወልደዋል የእባብን እንቍላል ቀፈቀፉ፥ የሸረሪትንም ድር አደሩ እንቍላላቸውንም የሚበላ ሰው ይሞታል፥ እንቍላሉም ሲሰበር እፉኝት ይወጣል። ድሮቻቸውም ልብስ አይሆኑላቸውም፥ በሥራቸውም አይሸፈኑም ሥራቸውም የበደል ሥራ ነው፥ የግፍም ሥራ በእጃቸው ነው። እግሮቻቸው ወደ ክፋት ይሮጣሉ፥ ንጹሑን ደም ለማፍሰስ ይፈጥናሉ አሳባቸው የኃጢአት አሳብ ነው፥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ በመንገዳቸው አለ። የሰላምን መንገድ አያውቁም፥ በአካሄዳቸውም ፍርድ የለም መንገዳቸውን አጣምመዋል፥ የሚሄድባትም ሁሉ ሰላምን አያውቅም።›› ኢሳ 592-8 እንደተባልነው ተጸጽተን በንስሐ መመለስ ይኖርብናል፡፡

ይቆየን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ:
-www.zeorthodox.org/ በቀሲስ ሶሎሞን ሙሉጌታ
-ሕግጋተ እግዚአብሔር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ 3ኛ
/ ትርጉም ቀሲስ እሸቱ ታደሰ/ ማኅበረ ቅዱሳን 1995 ዓ.ም



No comments:

Post a Comment